በተስፋለም ወልደየስ
በአማራ ክልል የሚገኙ ሚሊሺያዎች፣ ማናቸውም የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች እንዲሁም ለጦርነት ብቁ የሆኑ ወጣቶች ከነገ ሰኞ ሐምሌ 19፤ 2013 ጀምሮ በክልሉ በሚገኙ የወረዳ ማዕከላት እንዲገቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የክተት ጥሪ አቀረቡ። በክተት ጥሪው የሚሰባሰበው ኃይል አማራን እና መላውን ኢትዮጵያን በመታደግ ጦርነት ላይ እንደሚሳተፍም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
አቶ አገኘሁ ዛሬ እሁድ ረፋዱን በሰጡት መግለጫ፤ የህወሓት ኃይሎች እርሳቸው በሚመሩት ክልል ላይ “ወረራ” ፈጽመዋል ብለዋል። የወረራው ዋነኛ ዓላማ “የአማራ ህዝብን እንደ ህዝብ ለማዋረድ እና ለማጥፋት” ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህም ተሻግሮ “ኢትዮጵያን የማፍረስ” አጀንዳን ያነገበ ነው ብለዋል። “የአማራን ህዝብ ማጥቃት ኢትዮጵያን ማጥቃት ነው” ሲሉም አክለዋል።
“ይሄ ጦርነት ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ የተደገሰ ጦርነት ነው” ያሉት አቶ አገኘሁ፤ ዛሬ ያቀረቡት የክተት ጥሪ “የአማራ ህዝብን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ከመታደግ የሚመነጭ” እንደሆነ አስረድተዋል። “ሀገር የማፍረስ ዓላማ ያለው” ሲሉ የጠሩትን ኃይል፤ ህዝቡ “በተባበረ ክንድ እንዲደመስስ” ጥሪ አቅርበዋል።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ዛሬ ላቀረቡት የክተት ጥሪ “ሁሉም ሰው” አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በአማራ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ በኩል በ“ሰበር ዜና” የተላለፈው የዛሬው የክተት ጥሪ፤ በአማራ ክልል የሚገኝ “ማናቸውም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሃይል” የሚመለከት ነው ተብሏል።
“በክልላችን የሚገኝ የመንግስትን የጦር መሳሪያ የታጠቀ ሚሊሺያ፣ ሚሊሺያም ያልሆነ በሙሉ፣ በክልላችን ውስጥ የሚገኝ የግል ጦር መሳሪያ የታጠቁ በሙሉ፣ በክልላችን ውስጥ በሁሉም ቀበሌ ውስጥ የሚገኝ አካላዊ ሁኔታው ለግዳጅ፣ ለጦርነት ብቁ የሆነ ወጣት በሙሉ፣ ከነገ ጀምሮ በሁሉም የወረዳ ማዕከል እንዲከት ይህ የክተት ጥሪ ተላልፏል” ብለዋል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር።
በክልሉ ባሉ የወረዳ ማዕከላት የሚገቡ ታጣቂዎች፣ በግዳጅ የሚሰማሩበት ቀጠና ወይም ግንባር እንደሚነገራቸው አቶ አገኘሁ በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። በአማራ ክልል ያሉ “ተመላሽ የሰራዊት አባላት” እነዚህን ታጣቂዎች የ“መምራት፣ የማታገል እና የማዋጋት” ድርሻን የመወጣት ኃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑንም አስገንዘበዋል። የክልሉ ሁሉም የወረዳ እና የቀበሌ አስተዳደሮች ደግሞ ይህን ተግባር የማስተባበር ሚና እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል።
በዚህ ሳምንት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በአዛዥነት እንዲመሩ የተሾሙት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ለክልሉ ቴሌቭዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ በ“ወልድያም ሆነ በተለያዩ ከተሞች ከበቂ በላይ ኃይል አለ። ይኸ ኃይል ደግሞ መሰማራት በሚገባው፣ ማድረግ በሚገባው ተዘጋጅቶ ነው ያለው” ብለው ነበር። የልዩ ኃይል አዛዡ ሰራዊቱን “በተሻለ ደረጃ ሊመሩ የሚችሉ ጥሪውን ተቀብለው እየገቡ ነው። ወጣቱም ልዩ ኃይሉን ለማጠናከር በከፍተኛ [ደረጃ] ወደ ስልጠና ማዕከሎች ገብቷል” በማለት የክልሉ መንግስት ለሚቆጣጠረው የቴሌቭዥን ጣቢያ አብራርተዋል።
የአማራ ክልል “ማንኛውም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ኃይልን” ጦርነት እየተካሄደባቸው ወዳሉ ግንባሮች ለመላክ የወሰነው፤ በትግራይ በኩል ተመሳሳይ አካሄዶች ተግባር ላይ በመዋላቸው እንደሆነ አቶ አገኘሁ ጥቆማ ሰጥተዋል። “ወያኔ የሚከተለውን ስትራቴጂ ተጠቅመን እኛም ወያኔን እንፋለመዋለን” ሲሉ የተደመጡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፤ በዚሁ መግለጫቸው ሌላኛው ክፍል ላይ “ጠላት” ሲሉ የጠሩት ኃይል እየተጠቀመበት ነው ያሉትን አካሄድ አብራርተዋል።
“ጠላት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ነው በሁሉም አቅጣጫዎች ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው። በዚህ ጦርነት ከ12፣ 13 ዓመት ህጻናት እስከ 60 ዓመት አዛውንቶች የተሳተፉበት ነው። የትግራይ ህዝብ በዚህ ጦርነት ልጆቹን እያስጨረሰ ነው ያለው። ከግንባር በሚደርሰው መረጃ እና እየተደረገ ባለው ሪፖርት፤ እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ማዕበል (human wave) በመፍጠር፤ ጦርነት የማያውቁ ልጆች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ጉዳት እየደረሰባቸው ያለበት ሁኔታ ነው ያለው” ሲሉ ተፈላሚው ወገን እየተከተለ ነው ያሉትን አካሄድ አስረድተዋል።
የትግራይ ኃይሎች በአሁኑ ወቅት “ሙሉ በሙሉ የማጥቃት ሙከራ” እያደረጉ ያሉት በራያ ግንባር መሆኑን የጠቆሙት አቶ አገኘሁ፤ በጠለምት አካባቢም ተመሳሳይ ውጊያ እንዳለ አልሸሸጉም። በዋግ እና በወልቃይት አካባቢ ያለውን ሁኔታ “ትንኮሳ” በሚል አሳንሰውታል። በእነዚህ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ኃይል እና ሚሊሺያዎች በጋራ በመሆን “ጠላት” ያሉትን ኃይል በመፋለም ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ “የተቀናጀ ትግል” ሲሉ የጠሩት ውጊያ፤ በአፋር ክልል በኩልም እየተካሄደ መሆኑንም በዛሬው መግለጫቸው አንስተዋል። “እኛ ይሄ ኃይል ኢትዮጵያን የሚያፈርስ ነው ስንል ዝም ብለን አይደለም። የአፋርን እና የአማራን ህዝቦች በማንበርከክ ኢትዮጵያን የማፍረስ አጀንዳ ይዞ እየታገለ ነው ያለው” ሲሉም ውጊያው ከአንድ ክልል ተሻግሮ በመላው ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ መሆኑን አስገንዝበዋል።
“ይሄ ጠላት እስካልጠፋ ጊዜ ድረስ ከዚህ በኋላ እረፍት የለንም”
– አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር
የትግራይ ክልል ከአማራ እና አፋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች እየተጠናከረ የመጣው ውጊያ ያሳሰባቸው ወገኖች፤ ተፈላሚ ኃይሎች ጦርነት አቁመው ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ በተደጋጋጋሚ ቢወተውቱም እስካሁን ጥሪያቸው በይፋ ተቀባይነት አላገኘም። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የህወሓት ኃይልን በሚመለከት በዛሬው መግለጫቸው በተደጋጋሚ የተጠቀሙባቸው አገላለጾችም፤ የውይይት እና የድርድር ጥሪ አካሄዶችን ጥያቄ ውስጥ ያላስገባ ሆኗል።
“ይሄ ጠላት እስካልጠፋ ጊዜ ድረስ ከዚህ በኋላ እረፍት የለንም” ሲሉ አቶ አገኘሁ የክልላቸውን አቋም አሳውቀዋል። ዛሬ የተላለፈው የክተት ጥሪም እርሳቸው “የህወሓት ጁንታ” የሚሉትን ኃይል “ከምጽረ ገጽ ለማጥፋት” ያለመ መሆኑንም አበክረው ገልጸዋል። የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ በትላንትናው ዕለት ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫም፤ በተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ተብሎ የተሰየመውን ህወሓትን “ከምጽረ ገጽ ማጥፋት አለብን” ማለታቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)