በመቐለ ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ኮምቦልቻ ከተማ ገቡ

በበእምነት ወንድወሰን

በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከነበሩ 15 ሺህ ገደማ ተማሪዎች መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩት በትላንትናው ዕለት ክልሉን ለቅቀው በአፋር ክልል ወደሚገኘው ሰመራ ዩኒቨርስቲ መግባታቸውን ተማሪዎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ኮሚቴ፣ ተመላሽ ተማሪዎች እንዲሁም የሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና መምህራን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ተመላሽ ተማሪዎቹ ዛሬ ሰኞ ረፋዱን ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ጉዞ መጀመራቸውንም ገልጸዋል። 

ተመላሽ ተማሪዎቹ ሰመራ ዩኒቨርስቲ የደረሱት ትላንት እሁድ ከምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ እንደሆነ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አፋርን ከትግራይ ክልል ጋር በምታወስነው ኣብ አላ ከተማ ያሉ ሁለት ነዋሪዎች ተማሪዎችን የጫኑ 12 አውቶብሶች ትላንት ከቀኑ አስር ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ድረስ ከተማውን አቋርጠው ሲያልፉ ተመልክተናል ብለዋል። 

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን ለማስመለስ የተዋቀረው ኮሚቴ የቴክኒካል ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አባተ ጌታሁን፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትላንትናው ዕለት ሰመራ መግባታቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሆኖም በአካባቢው ካለው የደህንነት ስጋት አንጻር ተማሪዎቹን የማጓጓዝ ተግባር የተከናወነው በምሽት ሳይሆን በቀን እንደሆነ አስረድተዋል። 

በትግራይ ክልል በሚገኙት መቐለ፣ አዲግራት እና አክሱም ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ 15 ሺህ ገደማ ተማሪዎች እንደተመደቡ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በትላንትናው ዕለት ወደ ሰመራ የገቡት ተማሪዎች በመቐለ ዩኒቨርስቲ ይማሩ የነበሩት ብቻ እንደሆነ ዶ/ር አባተ ገልጸዋል። 

“ትናንት ያየነው ገና ጠብታ ነው። ገና ብዙ ሺህ ተማሪዎች በአዲግራት እና በአክሱም ይቀሩናል። እንቅልፍ አጥተን ነው ያለነው” ሲሉ የተማሪዎች አስመላሽ ኮሚቴ የቴክኒካል ክፍል ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ተመላሽ ተማሪዎቹ ዛሬ ሰኞ ረፋድ 4:30 ገደማ ላይ ሰመራ ዩኒቨርሲቲን ለቅቀው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ጉዞ መጀመራቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከራሳቸው ከተማሪዎቹ እና ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አረጋግጣለች። ተማሪዎቹ ዛሬ አመሻሹን ኮምቦልቻ ከተማ መግባታቸውን ምንጮች ተናግረዋል። ማንነታቸው እንዳይገለጽ የተናገሩ ሁለት ተመላሽ ተማሪዎች “የት እንደደረስንም ሆነ ሌላ መረጃ እንዳንሰጥ ትዕዛዝ ተሰጥቶን ነው እየተጓዝን ያለነው” በሚል ስለ አወጣጣቸውም ሆነ ስለ ጉዟቸው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች የትግራይ ክልልን ለቅቀው መውጣታቸውን በይፋ ከተነገረበት ከሰኔ 21፤ 2013 ጀምሮ፤ በክልሉ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ልጆች ይሏቸው ወላጆች ቅሬታቸውን በተለያየ መንገድ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩት የተማሪዎቹ ወላጆች በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት፣ በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ቢሮ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት በመገኘት፤ ልጆቻቸው በሰላም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ያደርጉ ዘንድ ተማጽኗቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ጭምር መግለጻቸው ይታወሳል። 

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል ያሉ ተማሪዎቹን ለማስመለስ ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዲሁም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር የተውጣጡ አባላት ያሉበት አብይ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ሲገልጽ ቆይቷል። 

የኮሚቴው አባላት የአፋር ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነችው ሰመራ ከተማ የገቡት ሰኔ 29፤ 2013 መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ተናግረዋል። ከኮሚቴው ጋር ለተማሪዎች ማጓጓዣ የተመደቡ 63 አውቶብሶች ወደ ሰመራ መግባታቸውንም ጠቁመዋል። ኮሚቴው ባለፈው ሐምሌ 6፤ 2013 መቶ ገደማ የሚሆኑ ተማሪዎችን ከመቐለ ዩኒቨርስቲ ማስመለስ መቻሉን ምንጮች አክለዋል።  (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)