እነ ጃዋር መሐመድ የፍርድ ቤት ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ተወሰነ

537

በሃሚድ አወል 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የተከሰሱ አራት ተከሳሾች፤ “በራሳቸው ፍቃድ ችሎት ፊት አንቀርብም” በማለታቸው ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ወሰነ። ከሳሽ ዐቃቤ ህግ አራቱ ተከሳሾች በተመጣጣኝ ኃይል ተገደው እንዲቀርቡ ወይም ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር። 

ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ የተወሰነው አራት ተከሳሾች ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ ናቸው። ተከሳሾቹ ለመጨረሻ ጊዜ ጉዳያቸውን ለመከታተል ፍርድ ቤት የቀረቡት ከሁለት ወራት በፊት ግንቦት 18 ፤2013 በዋለው ችሎት ነበር።

አራቱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ ያስታወቁት፤ ጉዳያቸውን እየተመለከተ ላለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ሰኔ 21፤ 2013 በጠበቆቻቸው በኩል ባቀረቡት ማመልከቻ ነበር። ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ላለመቅረብ የወሰኑት “በፍትህ ላይ በሚተወን ድራማ ላይ ተሳታፊ ላለመሆን” በሚል ምክንያት መሆኑን በዕለቱ የችሎት ውሎ በተነበበው ማመልከቻቸው መግለጻቸው ይታወሳል። 

ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 29 በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮም፤ አራቱ ተከሳሾች ተጨማሪ ማመልከቻ በማስገባት በውሳኔያቸው መጽናታቸውን አሳይተዋል። ተከሳሾቹ በሁለተኛው ማመልከቻቸው “ዐቃቤ ህግና ሌሎች የፍትህ አካላት የፍርድ ቤቶችን ውሳኔን በመፃረር፤ በነፃ የተሰናበቱ የፖለቲካ እስረኞችን አፍነው ወደ አልታወቀ ቦታ እየወሰዱ መሆናቸውን ስንመለከት በአጠቃላይ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ተስፋ እንድንቆርጥ እና ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል” ብለው ነበር። 

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 21፤ 2013 በዋለው ችሎት ተከሳሾች በአካል ቀርበው ችሎቱን ሂደቱን ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም አለመቅረባቸውን ገልጿል። ተከሳሾች ያቀረቡት አቤቱታ “የቀረበባቸውን ክስ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳይከራከሩ የሚያግድ አይደለም” ያለው ችሎቱ፤ አቤቱታቸው ከራሳቸው ጉዳይ ጋር “የሚገናኝ አይደለም” በሚል ውድቅ አድርጎታል።

እነ ጃዋር መሐመድ “ፍርድ ቤት አንቀርብም” ማለታቸውን ተከትሎ፤ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾቹ በተመጣጣኝ ኃይል ተገደው እንዲቀርቡ ወይም ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር። ፍርድ ቤቱም ተገደው እንዲቀርቡ የቀረበው ጥያቄ “የህግ አግባብ የለውም” በማለት፤ ችሎት አንቀርብም ያሉት ተከሳሾች በሌሉበት ክርክሩ እንዲቀጥል ወስኗል። 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች ስላለባቸው የደህንነት ስጋት ያቀረበውን መከራከሪያ በተመለከተ የተከሳሾችን መልስ ለመስማት ነበር። “የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ባለመተግበሩ ምክንያት ቀጠሮ እየተጓተተ ነው ያለው” ችሎቱ፤ በዐቃቤ ህግ መከራከሪያ ላይ የተከሳሾችን ምላሽ ለማድመጥ ለሐምሌ 30፤2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዛሬ ችሎት ፊት የቀረቡት ሌሎች ተከሳሾች በራሳቸው እና በጠበቆቻቸው በኩል አቤቱታዎችን ለችሎቱ አቅርበዋል። ተከሳሾቹ ያቀረቡት አቤቱታ “በምርመራ ወቅት በፌደራል ፖሊስ የተሰበሰቡ ንብረቶቻቸን አልተመለሱም፤ በፖሊስ እጅ የሚገኙት የተንቀሳቃሽ ስልኮቻችንም ክፍት ናቸው” የሚል ነው። የተከሳሾችን አቤቱታ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ በቃል የቀረቡት አቤቱታዎች ራሳቸውን ችለው መፍትሔ የሚፈልጉ በመሆናቸው በዝርዝር በጽሁፍ እንዲቀርቡ አዝዟል። 

በችሎት ከተገኙት ተከሳሾች ውስጥ ሁለቱ፤ የትዳር አጋሮቻቸው እንዲሁም እና ጫት ወደ ማረሚያ ቤት ማስገባት እንዲፈቅድላቸው በተጨማሪነት ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ በዚህኛው አቤቱታ ላይ ምንም አይነት አስተያየት ሳይሰጥ አልፎታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)