ወልድያ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎቹን በነገው ዕለት ሊሸኝ ነው

659

በበእምነት ወንድወሰን

በወልድያ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 200 ገደማ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች በነገው ዕለት ወደ ሰመራ ዩኒቨርስቲ ሊሸኙ ነው። ዩኒቨርስቲው ተማሪዎቹን ለመሸኘት የወሰነው፤ ለመጀመሪያ ዓመት እና ነባር የጤና ሳይንስ ተማሪዎቹ ከትላንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ እረፍት መስጠቱን በይፋ ማሳወቁን ተከትሎ ነው። 

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበበ ግርማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዛሬ ረቡዕ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ባለው ጦርነት የደህንነት ስጋት በመኖሩ ተማሪዎቹ ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ከውሳኔ ላይ መደረሱን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ የቀሩትን የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎችን፤ በሰመራ በኩል ወደ ትግራይ ለመሸኘት መወሰኑን አስታውቀዋል።  

በወልድያ አካባቢ እየተባባሰ የመጣውን ውጊያ በመስጋት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ግቢውን ለቅቀው መውጣት የጀመሩት ካለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 17 ጀምሮ ነበር። በርካታ ተማሪዎች በራሳቸው ውሳኔ ዩኒቨርስቲውን ለቅቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄዳቸው፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን እንዳስተጓጎለው የወልዲያ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሱልጣን መሐመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ ወልድያ ዩኒቨርስቲ

የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን ከሶስት ሳምንት በፊት የተቀበለው የወልድያ ዩኒቨርስቲ፤ የመማር ማስተማር ሂደቱን በትላንትናው ዕለት በይፋ ከሟቀረጡ በፊት ለአዲስ ገቢዎች እና ለነባር የጤና ሳይንስ ተማሪዎች ትምህርት በመስጠት ላይ እንደነበር ዶ/ር ሱልጣን ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ከእነዚህ ተማሪዎች በተጨማሪ፤ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ባለፈው ሐምሌ 10 የተመረቁ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች “ክሊራንስ” ለመጨረስ እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ በግቢው ውስጥ ነበሩ ብለዋል። 

ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት የተቀበላቸው 12,500 ተማሪዎችን ሲሆን ነባር ተማሪዎቹን ለክረምት እረፍት ያሰናበተው ሰኔ 30፤ 2013 ነበር። ዩኒቨርስቲው ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 20 ባወጣው ማስታወቂያ ደግሞ፤ በዚህ ወቅት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሁሉም ተማሪዎች “ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲሄዱ የእረፍት ጊዜ መስጠቱን” አስታውቋል። 

ፎቶ፦ ወልድያ ዩኒቨርስቲ

ከዚህ ማስታወቂያ መውጣት በኋላ በግቢው ውስጥ የቀሩ 200 ገደማ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎችን ዕጣ ፈንታ በተመለከተ፤ ዩኒቨርስቲው ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር መወያየቱን የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ይናገራሉ። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ሰመራ ዩኒቨርስቲ ካደረሰ በኋላ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተወካዮች ተማሪዎቹን ለመረከብ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ያስረዳሉ። 

በዚህም ስምምነት መሰረት የወልድያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹን በነገው ዕለት ወደ ሰመራ ዩኒቨርስቲ ለማጓጓዝ አራት የራሱን አውቶብሶች መመደቡን ዶ/ር አበበ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳደር” ገልጸዋል። በአካባቢ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያትም ተማሪዎቹ በወሎ አድርገው ሰመራ እስከሚገቡ ድረስ በመከላከያ ሰራዊት እና በአማራ ክልል ልዩ ኃይል እጀባ እንደሚደረግላቸው አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)