ኢዜማ ምርጫ እንዲደገም የጠየቀባቸውን የምርጫ ክልሎች በተመለከተ፤ ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥ ፍርድ ቤት ወሰነ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በ28 ምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ እንዲደገም ላቀረበው አቤቱታ፤ ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥ በፍርድ ቤት ተወሰነ። ውሳኔውን ዛሬ ሐሙስ 22 ያሳለፈው፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ የምርጫ ጉዳይ ችሎት ነው።

የኢዜማን ይግባኝ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ያደመጠው የምርጫ ጉዳይ ችሎቱ፤ ምርጫ ቦርድ ለቀረበው አቤቱታ “መልስ መስጠት ይገባዋል ወይስ አይገባውም” በሚለው ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነበር ለዛሬ ቀጠሮ የሰጠው። ችሎቱ ዛሬ በጽህፈት ቤት በኩል በሰጠው ውሳኔ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሹን ለሐምሌ 30፤ 2013 በጽሁፍ እንዲያቀርብ አዝዟል። 

ኢዜማ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስገባው ባለ 12 ገጽ አቤቱታ፤ በደቡብ ክልል በሚገኙ 28 የምርጫ ክልሎች ላይ ከምርጫ ጣቢያዎች አከፋፈት፣ ከድምፅ አሰጣጥ፣ ከድምፅ ቆጠራና ማዳመር እና ከድምፅ መስጫ ወረቀቶች ህትመት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በዝርዝር አቅርቧል። እኒህን ችግሮች በቅድሚያ ለምርጫ ቦርድ አቅርቦ እንደነበር የጠቆመው ኢዜማ፤ ሆኖም ቦርዱ የፓርቲውን አቤቱታ ያጣራበት እና የመረመረበት አግባብ ላይ ቅሬታ እንዳለው ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል። 

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው ውሳኔው፤ ኢዜማ አቤቱታውን ለምርጫ ቦርዱ ያቀረበበት የቅሬታ ማቅረቢያ ቅጽ እንዲቀርብለት ተጨማሪ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ከተካሄደ ከአራት ቀናት በኋላ ለምርጫ ቦርድ ቀርቧል የተባለው የኢዜማ አቤቱታ፤ 68 የምርጫ ክልሎችን የተመለከተ ነበር። 

ሆኖም ፓርቲው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሲወስድ፤ “ከበቂ በላይ ማስረጃ አቅርቤባችኋለሁ” ባላቸው እና በደቡብ ክልል በሚገኙ 28 የምርጫ ክልሎች ላይ ብቻ መወሰነን መርጧል። ኢዜማ በደቡብ ክልል ምርጫ ከተከናወነባቸው 85 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ አራት መቀመጫዎችን ማሸነፉ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)