በእስር ላይ የሚገኙት 13 ጋዜጠኞች፤ በፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ለመቅረባቸው ማስረጃ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ

በሃሚድ አወል

በእስር ላይ የሚገኙት 13 የአውሎ ሚዲያ እና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች፤ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው በአዋሽ ሰባት ኪሎ በሚገኝ ፍርድ ቤት እየቀረቡ ስለመሆኑ ማስረጃ እንዲቀርብ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። በአፋር ክልል ፈንታሌ ወረዳ የሚገኘው ይኸው ፍርድ ቤት የተጠርጣሪዎችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ እየተመለከተ ለመሆኑም ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብም ታዝዟል። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ የፍትሃ ብሔር ችሎት የጋዜጠኞቹን ጉዳይ መመልከት የጀመረው፤ በአስራ ሶስቱ ጋዜጠኞች ጠበቃ በኩል “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ ከቀረበለት በኋላ ነው። ችሎቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ፤ የፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ፍቃድ የሰጠበትን ሰነድ እንዲያቀርብ ነበር።

በዚህም መሰረት የፌደራል ፖሊስ፤ የፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 26 ድረስ ለሁለት ጊዜ የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ የፈቀደለት መሆኑን የሚያሳይ ደብዳቤ ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል። ለፍርድ ቤት በቀረበው ሰነድ ላይም፤ በ14ቱ ተጠርጣሪዎች ላይ በሁለት መዝገብ ተከፍሎ ሰኔ 29፤ 2013 የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ መከፈቱ ተመላክቷል።

የፌደራል ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ሰነድ መሰረት በጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ስም በሚጠራው የመጀመሪያው መዝገብ ሰባት ተጠርጣሪዎች ተካትተዋል። በሙሴ ሀደራ በሚጠራው መዝገብ ደግሞ ሌሎች ሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። በዚሁ መዝገብ ጸጋዘአብ ኪዳኔ የተባለ “አክቲቪስት” መካተቱም ተገልጿል።  

ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ወንጀል ነው። በዛሬው የችሎት ውሎ የተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ታደለ ገብረመድህን “ፖሊስ ያቀረበው የጊዜ ቀጠሮ መሰጠቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ብቻ ነው። የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ አላቀረበም’’ ሲሉ ተከራክረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፖሊስ ባቀረበው ሰነድ መሰረት፤ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ሐምሌ 12 የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት የቀረቡት ግን ሐምሌ 19 መሆኑ በሰነዱ ላይ መጻፉን ጠበቃው ጠቅሰዋል።  

ለጠበቃው መከራከሪያ ምላሽ የሰጠው የፌደራል ፖሊስ፤ በሰነዱ ላይ የተጠቀሰው ቀን የፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ደብዳቤውን ለፌደራል ፖሊስ የፃፈበት እንጂ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት የቀረቡበት አይደለም ብሏል። የወረዳው ፍርድ ቤት ደብዳቤውን ሐምሌ 19 ይጻፈው እንጂ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሐምሌ 12 ነው ሲል ተከራክሯል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የቀጠሮው ቀን ሐምሌ 12፤ 2013 ሆኖ “ለምን ሐምሌ 19 ችሎት እንደተሰየመ ግልጽ አይደለም” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። የፍትሃ ብሔር ችሎቱ ከፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት የሚቀርብለትን ምላሽ ለመመልከት ለሐምሌ 29፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን ውሎ አጠናቅቋል። 

በአዋሽ ሰባት ኪሎ በእስር ላይ የሚገኙት አስራ አንዱ የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች በፖሊስ የተያዙት ሰኔ 22፤ 2013 ነው። የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች የሆኑት አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ ደግሞ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 24 እና 25 መሆኑን ጠበቃቸው አቶ ታደለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)