ባልደራስ በአዲስ አበባ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ እንደሚፈልግ አስታወቀ

* በምርጫው ላይ ያቀረበውን አቤቱታ ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱንም ገልጿል 

በሃሚድ አወል 

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በአዲስ አበባ በ21 ምርጫ ክልሎች በድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ እንደሚፈልግ አስታወቀ። የሃያ አንዱን የምርጫ ክልሎች የምርጫ ውጤት እንደማይቀበል የገለጸው ፓርቲው፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደውም ይፋ አድርጓል። 

ፓርቲው ይህን አቋሙን ያሳወቀው በአዲስ አበባ ከተማ የነበረውን የምርጫ እና ድህረ ምርጫ ሂደትን በተመለከተ የሰራውን የግምገማ ውጤት ዛሬ አርብ ሐምሌ 23፤ 2013 ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። የባልደራስ ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ “ይኼ ምርጫ፤ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ hijack ተደርጓል። ስለዚህ የምርጫውን ውጤት በፍጹም አንቀበለውም” ሲሉ በፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ባልደራስ፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ “የነጻ ምርጫን ዝቅተኛ መስፈርቶች ያላሟላ ነበር” ሲል በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፤ በዛሬው መግለጫውም ይህንኑ በድጋሚ አስተጋብቷል። ፓርቲው ይህን አቋሙን በቅድመ ምርጫ ወቅት ጭምር በይፋ ሲያሳውቅ ቢቆይም ሰኔ 14፤ 2013 በተካሄደው ምርጫ ላይ ግን ከመሳተፍ ወደ ኋላ አላለም። 

ባልደራስ በአዲስ አበባ ከተማ ለተወካዮች ምክር ቤት እና ለከተማይቱ ምክር ቤት የተወዳደሩ በድምሩ 161 ዕጩዎችን አቅርቧል። ከተማይቱ ባሏት 23 ምርጫ ክልሎች በሙሉ ዕጩዎችን ያቀረበው ባልደራስ፤ በሃያ አንዱ ምርጫ ክልሎች ላይ ነበሩ ያላቸውን ችግሮችን ለኢትዮጵያ ብሔራው ምርጫ ቦርድ ማስገባቱን ገልጿል። ፓርቲው በአዲስ አበባ ቅሬታ ያላቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ምርጫ ክልል 15 እና ምርጫ ክልል 2/14 መሆናቸውን የፓርቲው ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢገልጹም፤ ምክንያቱን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።  

በሰው እና የሰነድ ምስክሮች የተደገፈ ነበር የተባለው የፓርቲው ዝርዝር አቤቱታ፤ በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ምርጫ ቦርድ አቤቱታውን ሳይቀበለው የቀረው “ቅሬታው የምርጫ ውጤቱን አይቀይረውም በሚል የተዛባ እሳቤ” ነው ሲል ባልደራስ በዛሬው መግለጫው ላይ ተችቷል። 

ፓርቲው በምርጫ ቦርድ ውድቅ የተደረገበትን አቤቱታ ይዞ ለፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱንም በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቁሟል። ባልደራስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው “በፍትህ ስርዓቱ ገለልተኛ ዳኝነት አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን የአዲስ አበባን ሕዝብ ስለ ምርጫ ቦርድ እና ስለ ፍትህ ስርዓቱ ገለልተኛ አለመሆን በተግባር የተደገፈ ግንዛቤ እንዲያገኝ ለማስቻል ነው” ሲል ፓርቲው አስገንዝቧል። 

ባልደራስ ለፍርድ ቤት ላቀረበው አቤቱታ የጠየቀው ዳኝነት ምን እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ፤ “በሃያ አንዱም ምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ነው የምንፈልገው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

ተቃዋሚ ፓርቲው ለፍርድ ቤት ማስገባቱን ከገለጸው ዝርዝር አቤቱታ ባሻገር፤ በ30 ገጾች የተዘጋጀ የምርጫ ግምገማ ጥናትን በዛሬው መግለጫ ይፋ አድርጓል። የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ “አሁን ይኼ ጥናት የሚቀርብበት ሰዓት አይደለም። የክተት አዋጅ ታውጆ ስለምርጫ ማውራት ቅንጦት ነው። ነገር ግን ዝም ማለታችን ለደጋፊዎቻችን ውጤቱን አምነን የተቀበልን ይመስላል። ደጋፊዎቻችን እንዲያዝኑ አንፈልግም” ሲሉ የግምገማ ውጤቱ የቀረበበትን ምክንያት ተናግረዋል። 

የግምገማ ጥናቱ “በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በምርጫ ሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን ነቅሶ ማውጣት እና በድህረ ምርጫ ባሉት ቀናት የታዩ ተግዳሮቶችን የሚገመግም ነው” ሲል ፓርቲው ስላዘጋጀው ሰነድ ምንነት አብራርቷል። በባልደራስ ዝርዝር ጥናት፤ የድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት፣ የድምጽ ቆጠራ ሂደት፣ ቅሬታን ለመግለጽ የነበረው ስነ ስርዓት፣ በፓርቲ ወኪሎች እና ታዛቢዎች ላይ የደረሰው ጫና፣ የምርጫ ህጉ እና ስነ ስርዓቱ እንዲሁም የድህረ ምርጫ ቅሬታ አቀራረብ ተዳስሰዋል። 

የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን በተመለከተ ፓርቲው በግምገማ ሰነዱ ላይ በዋነኛነት የተቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችን ነው። የምርጫ አስፈጻሚዎች “በብቃታቸው ሳይሆን በማንነታቸው መመልመላቸው ምርጫው ነጻ እና ፍትሐዊ እንዳይሆን አድርጎታል” ሲል ወንጅሏል። የምርጫ አስፈጻሚዎቹ “የድምጽ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱን ጠንቅቀው የማያውቁ ናቸው” በማለትም ተችቷል። 

ከድምጽ አሰጣጥ ሂደት ጋር በተያያዘ ባልደራስ ክስ የሰነዘረበት ሌላው አካል ገዢው የብልጽግና ፓርቲን ነው። ገዢው ፓርቲ፤ ምርጫው የግለሰብ ነጻ ፍላጎት የሚገለጽበት ሳይሆን “የቡድን ምርጫ በማድረግ የዜጎችን መብት ሲጋፋ ታይቷል” ሲል ባልደራስ ወቅሷል። ገዢው ፓርቲ ስልጣንን እና የሕዝቡን ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም በመጠቀም ድምጽ ለማግኘት ተጠቅሞበታል ሲል የወነጀለው ፓርቲው፤ “ብልጽግና በቅስቀሳ ጊዜ የተጠቀመበት በኋላም ከድጎማ እና ከማባባያ ጋር አቀናጅቶ የተጠቀመበት የ1 ለ10 አደረጃጀት በምርጫው ወቅት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል” ብሏል። 

የድምጽ መስጫው ዕለት የብልጽግና ታዛቢዎች በምርጫ ወቅት የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደነበርም ባልደራስ በጥናቱ ላይ ጠቁሟል። “በአንዳንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የብልጽግና ዕጩዎች በምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ በመግባት ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ነበር” ሲልም ፓርቲው ተጨማሪ ውንጀላ አክሏል። ሰኔ 14፤ 2013 ተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ምስጢራዊነቱ ያልተጠበቀ መሆኑን በግምገማው የሚያነሳው ባልደራስ፤ የ“ብልጽግና አመራሮች እና ምርጫ አስፈጻሚዎች የድምጽ አሰጣጡን ሚስጢራዊነት በተደጋጋሚ ሲጥሱት እንደነበር” በጥናት እንደደረሰበት አስታውቋል።

ባልደራስ በግምገማ ውጤቱ የዳሰሰው ሌላው ጉዳይ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት እና የህትመት ችግር ነው። “በድምጽ መስጫ ዕለት ከፍተኛ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እጥረት ተስተውሏል” ብሏል። የህትመት ችግርን በተመለከተም ባልደራስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረባቸው አንድ ዕጩ ላይ የደረሰውን በምሳሌነት ጠቅሷል። ፓርቲው ለፓርላማ በዕጩነት ያቀረባቸው ወ/ሮ አስቴር ስዩም በድምጽ መስጫ ወረቀት ላይ ሳይካተቱ ቀርተዋል ብሏል።     

የተቃዋሚ ፓርቲው በግምገማው ካነሳቸው ጉዳዮች መካከል የድምጽ ቆጠራው ላይ የተፈጠሩ ሳንካዎች ይገኙበታል። “ድምጽ አልባ ወረቀቶች ለብልጽግና እንዲቆጠሩ ተደርገዋል” ሲል ቅሬታውን በግምገማው ያሰፈረው ባልደራስ፤ ለዚህም በአራት ምርጫ ጣቢያዎች የነበሩ መሰል ክስተቶችን በማሳያነት አንስቷል።

“በርከት ካሉ ምርጫ ጣቢያዎች ከተገኙ መረጃዎች መረዳት እንደተቻለው፤ በተለያዩ ምክንያቶች በትክክል ምልክት ያልተደረገባቸው የምርጫ ወረቀቶች ለብልጽግና እንዲቆጠሩ ተደርገዋል” ሲል ባልደራስ በጥናቱ ላይ ክሱን አቅርቧል። ከዚህ በተጨማሪም በድምጽ ቆጠራው ጊዜ የፓርቲ ወኪሎች እንዲወጡ ተደርገዋልም ብሏል። 

በድምጽ መስጫ ዕለት የነበረው የቅሬታ አገላለጽ በፓርቲው ግምገማ የተነሳው ሌላኛው ጉዳይ ነው። ፓርቲው “በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች ቅሬታ ሰሚ ባለመኖሩ ምርጫው ላይ ለሚነሱ ቅሬታዎች መልስ ማግኘት አልተቻለም” ሲል በዕለቱ ነበረ ያለውን ችግር አመልክቷል። በፓርቲ ወኪሎች እና ታዛቢዎች ላይ ጫና መድረሱ፣ ድብደባ መከናወኑ እና በገንዘብ የመደለል ሙከራዎች እንደነበሩም ባልደራስ በጥናቱ አትቷል።

ፓርቲው ሌላው በጥናቱ ያነሳው ጉዳይ የታዛቢዎችን ጉዳይ ነው። “በ1997 ምርጫ በህዝብ የተመረጡ ግለሰቦች ምርጫውን እንዲታዘቡ ይመረጡ ነበር” የሚለው ባልደራስ፤ በሰኔ 14ቱ ምርጫ ግን “በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በሚባል ደረጃ የህዝብ ታዛቢዎች አልነበሩም” ብሏል። የህዝብ ታዛቢዎች በስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ የመሳተፍ እድል አለመሰጠቱ፤ “የምርጫ ቦርድ እና የብልጽግና የፖለቲካ ሸፍጥ ነው” ሲል ባልደራስ ወንጅሏል። 

በምርጫ ቦርድ ላይ በተቃዋሚ ፓርቲው የተሰነዘረው ውንጀላ ምርጫ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቱ “ለብልጽግና ፓርቲ የወገነ ነው” እስከሚል ድረስ የተሻገረ ነው። “ምርጫ ቦርድ ለገዢው ፓርቲ የወገነና ነጻ እና ገለልተኛ አካል አለመሆኑን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ተገንዝቧል” ብሏል ፓርቲው። 

“በድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ የታዩት ችግሮች፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት እጥረት እና የተሳሳቱ የምርጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተፈጠሩ ክፍተቶች ሳይሆኑ ቀደም ሲል የታሰበባቸው ክንውኖች ነበሩ” ሲልም ባልደራስ ተጨማሪ ክስ አቅርቧል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በምርጫ ሂደቱ ላይ ያቀረባቸውን ችግሮች እና በምርጫ ቦርድ ላይ የሰነዘራቸውን ውንጀላዎች በተመለከተ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)