በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ላይ የተመሰረተውን ክስ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

በሃሚድ አወል 

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ ስር የተካተቱ 62 ተከሳሾች ላይ የተመሰረተውን ክስ ለመስማት ለነሐሴ 11 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮውን የሰጠው የዐቃቤ ህግ ማስረጃ ተሟልቶ አለመቅረቡን እና ክሱ ሰፊ መሆኑን በመጥቀስ ነው። 

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በ62ቱ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ላይ ክስ መመስረቱን ያስታወቀው ሐምሌ 16 ሲሆን፤ ጉዳዩ ለዛሬ የተቀጠረው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾች በችሎት በተገኙበት ክሱን ለማንበብ ነበር። በዛሬው የችሎት ውሎ አቶ ስብሃት ነጋ እና ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሂምን ጨምሮ 19 ተከሳሾች ችሎት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እና የሰነድ ማስረጃዎችን ቢቀበሉም ክሱ ሳይነበብ ቀርቷል። 

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የመሰረታቸውን ሁለት ክሶች ለማስረዳት 510 የሰው ምስክሮችን እና እና 5,329 የገጽ ብዛት ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎችን በማያያዝ ለፍርድ ቤት ማቅረቡን ከዚህ ቀደም የገለጸ ቢሆንም፤ “በፍላሽ እጥረት ምክንያት ልዩ ማስረጃዎችን አላቀረብንም” ሲል በዛሬው የችሎት ውሎ ተናግሯል። ልዩ ማስረጃዎችን በቀጣይ ቀጠሮ ይዞ እንደሚቀርብም አስታውቋል። 

ይህ የዐቃቤ ህግ ገለጻ ግን በተከሳሽ ጠበቆች ተቃውሞ ገጥሞታል። “[ዐቃቤ ህግ] ክስ ሲመሰርት፤ ክሱንም ማስረጃውንም ለፍርድ ቤት ማቅረብ ነበረበት” ያሉት ጠበቆቹ፤ ክሱ ካልተሟላ ወደ ቀጣይ ሂደት መሄድ እንደማይችሉ ለችሎቱ አስረድተዋል። 

ጉዳዩን ያደመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ- ሽብርና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ ያላሟላውን የምስል ማስረጃ ከቀጠሮ ቀን በፊት አሟልቶ በፍርድ ቤት ጽህፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይኸው ማስረጃ ለተከሳሾችም በጠበቆቻቸው በኩል እንዲደርሳቸው አዝዟል።

በዛሬው ችሎት በሌሉበት የተከሰሱ ግለሰቦች ጉዳይም ተነስቷል። በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን መዝገብ የተካተቱ አብዛኞቹ ተከሳሾች በሌሉበት የተከሰሱ ሲሆን፤ የፌደራል ፖሊስ ለእነዚሁ ተከሳሾች መጥሪያ በማድረስ በዛሬው ቀጠሮ በአካል እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ባስገባው ደብዳቤ “የተከሳሾች አድራሻ ትግራይ ክልል በመሆኑ እና በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ” ምክንያት ተከሳሾችን ማቅረብ እንዳልቻለ አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪም በማረሚያ ቤት ከሚገኙ ተከሳሾች ውስጥ የ59ኛ እና 62ኛ ተከሳሾች ስም ዝርዝር ባለመካተቱ ፍርድ ቤት ማቅረብ እንዳልቻለ በችሎት የተገኙ የማረሚያ ቤት ተወካይ አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ የዛሬ ውሎዉን ከማጠናቀቁ በፊት በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤት ያልቀረቡት አቶ ዶሪ አስገዶም እና አምባሳደር አባይ ወልዱ በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)