በአክሱም ዩኒቨርስቲ ተመድበው ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎችን ማስወጣት ተጀመረ

– የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የማስወጣት ሂደት ተጠናቅቋል ተብሏል

በበእምነት ወንድወሰን

በትግራይ ክልል በሚገኘው አክሱም ዩኒቨርስቲ ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ ተማሪዎች መካከል፤ ግማሽ ያህሉ ትላንት ምሽት በአፋር ክልል ወደሚገኘው ሰመራ ዩኒቨርስቲ መግባታቸውን ተመላሽ ተማሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ማስወጣት የተጀመረው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎችን የመመለስ ሂደት ባለፈው አርብ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአክሱም ዩኒቨርስቲ ተመድበው ሲማሩ የቆዩ ተማሪዎች ብዛት 3,500 እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ አስታውቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ ትላንት ሰኞ ሐምሌ 26 ወደ አፋር ክልል የገቡት 1,820 ተማሪዎች መሆናቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ተመላሽ ተማሪዎች ተናግረዋል። 

ፎቶዎች፦ ከአክሱም ዩኒቨርስቲ ፋይል የተወሰዱ

ተማሪዎቹ አፋር እና ትግራይን በምታዋስነው “መዝአለት” በተባለች አነስተኛ ወረዳ ላይ ሲደርሱ ተማሪዎቹን ለማስመለስ የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት እንደተቀበሏቸው ገልጸዋል። የኮሚቴው አባላት “ቀጣይ ጉዞአችሁ የት እንደሚሆን እና አንዳንድ የሚሞሉ ፎርሞችን ነገ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይሰጣችኋል” ሲሉ እንደነገሯቸውም ተመላሽ ተማሪዎቹ አስረድተዋል። 

አፋርን ከትግራይ በምታዋስነው አብኣላ ከተማ የሚኖሩ አራት የከተማው ነዋሪዎች፤ ተማሪዎችን የጫኑ ከ20 የሚበልጡ አውቶብሶች ትናንት ማምሻውን ከተማውን ሲያቋርጡ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የዓይን እማኞች በበኩላቸው የአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በ28 አውቶብሶች ተጭነው ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የደረሱት ትናንት ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ ነው ብለዋል። 

በትግራይ ክልል ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ያሉ ተማሪዎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ፤ በአክሱም ዩኒቨርስቲ ያሉ ተማሪዎችን በሁለት ዙር ለመመለስ 60 አውቶብሶችን አዘጋጅቶ ሲጠባበቅ እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭ አመልክተዋል። የማስመለስ ሂደቱን ከተቻለ በሁለት ቀን ለማጠናቀቅ እቅድ እንዳለም ጠቁመዋል።

ኮሚቴው በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ መልሶ ለመጨረስ ሶስት ሳምንት ፈጅቶበታል። በተለያዩ ዙሮች የተከፋፈለው የማስመለስ ሂደት ባለፈው አርብ ሐምሌ 23፤ 2013 መጠናቀቁን የኮሚቴ የቴክኒካል ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አባተ ጌታሁን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ተማሪዎቹን ወደ የአካባቢያቸው ለማስመለስ “ከፍተኛ ዋጋ እየተከፈለ ነው” ያሉት ኃላፊው፤ በተቀሩት ዩኒቨርሲቲዎች “ከመጀመሪያው ዙር የበለጡ ተማሪዎች ይጠብቁናል” ብለዋል።  

በትግራይ ክልል በሚገኙት መቐለ፣ አዲግራት እና አክሱም ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የክልሉ ተወላጅ ያልሆኑ 15 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ከሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ እስካሁን ምን ያህሉ እንደተመለሱ ለማረጋገጥ፤ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ሆነ ተማሪዎቹን ለማስመለስ ለተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ ጥያቄዎች ብናቀርብም፤ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)