በሃሚድ አወል
ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣም ውሳኔ አስተላልፏል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳይ ችሎት ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 27፤ 2013 ውሳኔውን የሰጠው፤ ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸውን ሶስት የቅጣት ማክበጃዎች በመቀበል ነው። ዐቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በጋራ መሆኑን፣ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ወንጀሉን የፈጸሙት በሌሊት ጨለማን ተገን በማድረግ፣ የጦር መሳሪያ በመያዝ መሆኑን በቅጣት ማክበጃነት አቅርቧል። ሁለቱ ተከሳሾች ግድያውን የፈፀሙት ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ መሆኑን በተጨማሪ የቅጣት ማክበጃነትም ጠቅሷል።
ዐቃቤ ህግ ሐምሌ 8፤ 2013 ለፍርድ ቤት ባቀረበው የቅጣት አስተያየት አንደኛ ተከሳሽ ድርጊቱን የፈፀመው “ታዋቂ የኦሮሞ ሰዎችን በመግደል መንግስትን ከስልጣን ለመጣል እና ለማሸበር በማሰብ ነው’’ ብሎ ነበር። “ተከሳሽ ያለመው ተሳክቶለት ህዝብ በህዝብ ላይ በመነሳት፤ በአዲስ አበባ የ13፤ በኦሮሚያ ደግሞ የ167 ሰው ህይወት ጠፍቷል’’ ያለው ዐቃቤ ህግ፤ ከተከሳሽ ድርጊት እና ካስከተለው ውጤት አንፃር የሞት ቅጣት ይወሰንበት ሲል ጠይቆ ነበር።
የተከሳሽ ተከላካይ ጠበቃ በበኩላቸው ተከሳሽ በባጃጅ ስርቆት ቢጠረጠርም በፍርድ ቤት ጥፋተኛ አልተባለም ሲሉ ተከሳሽ ከዚህ በፊት “ምንም አይነት የወንጀል ሪከርድ” የለበትም በማለት ተከራክረዋል። በተጨማሪም “የሞት ቅጣት የሚጠየቀው ምንም አይነት የቅጣት ማቅለያ ካልቀረበ ብቻ ነው” በማለት ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ህግ የጠየቀውን የሞት ቅጣት ውድቅ እንዲያደርገው ጠይቀዋል።
አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች በበኩላቸው የበፊት ባህሪያቸው መልካም መሆኑን፣ ግድያውን የፈጸሙት ባለመማራቸው እንደሆነ፣ እድሜያቸው ወጣት በመሆኑ ለአገር ልማት አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ፣ በሚኖሩበት አካባቢ በበጎ አድራጎት ሲሳተፉ መቆየታቸውን፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እና ችሎቱን በመልካም ባህሪ ሲከታተሉ መቆየታቸውን በቅጣት ማቅለያነት አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች “ከዚህ በፊት መልካም ባህሪ ነበረን’” በሚል ያቀረቡትን የቅጣት ማቅለያ ቢቀበልም፤ ቀሪዎቹን የቅጣት አስተያየቶች ውድቅ አድርጎባቸዋል። “ችሎት በመልካም ባህሪ ስንከታተል ነበር” የሚለው የተከሳሾችን የቅጣት አስተያየት፤ “የተከሳሾች ግዴታ ነው” ሲል ችሎቱ አልተቀበለውም። በተጨማሪም ተከሳሾቹ “ወጣት ነን” ሲሉ ያቀረቡት አስተያየት፤ ችሎቱን ባለማሳመኑ እና በሌሎቹ የቅጣት ማቅለያዎች ላይ ተከሳሾች ማስረጃ ባለማቅረባቸው ችሎቱ አለመቀበሉን ገልጿል።
የዐቃቤ ህግን ሶስት የቅጣት ማክበጃዎች እና የተከሳሾችን አንድ የቅጣት ማቅለያ የተቀበለው ፍርድ ቤቱ፤ ተከሳሾች እጃቸው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በሚቆጠር አንደኛ ተከሳሽ በዕድሜ ልክ እስራት ሁለተኛ ተከሳሽ ደግሞ በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል። ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎው በሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ ላይም የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።
ሶስተኛው ተከሳሽ በወንጀሉ ላይ የድርጊት ተሳትፎ የሌለው በመሆኑ የስድስት ወራት እስራት መፍረዱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ሆኖም ተከሳሹ ከተፈረደበት ወራት በላይ በእስር በማሳለፉ፤ የሚፈለግበት ሌላ ወንጀል ከሌለ በስተቀር ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)