ድጋሚ ቆጠራ እንዲከናወን ከተወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች፤ በሁለቱ የተካሄደው ቆጠራ ተጠናቀቀ

በሃሚድ አወል  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድጋሚ ቆጠራ እንዲከናወን ባዘዛባቸው አምስት የምርጫ ክልሎች ቆጠራ መካሄዱን የቦርዱ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድጋሚ ቆጠራ እንዲከናወን ከወሰነባቸው አስር የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሁለት ምርጫ ክልሎች ቆጠራ ሲጠናቀቅ፤ በሶስት ምርጫ ክልሎች ላይ ቆጠራው ተጀምሯል ተብሏል።     

ምርጫ ቦርድ አጠቃላይ የምርጫውን ውጤት ይፋ ባደረገበት ሐምሌ 3፤ 2013፤ ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ የአሰራር ግድፈቶችን መርምሮ እርምጃ መውሰዱን አስታውቆ ነበር። ቦርዱ “የአሰራር ግድፈት ተስተውሎባቸዋል” በተባሉት ምርጫ ክልሎች ላይ የድጋሚ ቆጠራን እና ድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን ማዘዙም የሚታወስ ነው።    

የድጋሚ ቆጠራ እንዲካሄድ ከተወሰነባቸው አስር የምርጫ ክልሎች ውስጥ ሶስቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ የተከናወነባቸው ናቸው። የፓርላማ ምርጫ የተከናወነባቸው እነዚህ የምርጫ ክልሎች፤ በደቡብ እና አማራ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የሚገኙ ናቸው። 

በደቡብ ክልል፣ ባኮ ጋዘር 1 የምርጫ ክልል እንዲደረግ የተወሰነው ድጋሚ ቆጠራ፤ ባለፈው ሳምንት አርብ ተጀምሮ ዛሬ ማክሰኞ መጠናቀቁን የምርጫ ቦርድ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሬው በቀለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኘው በባኮ ጋዘር 1 ምርጫ ክልል ለፓርላማ መቀመጫ ለመወዳደር ዕጩዎችን ያቀረቡት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸውን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል። ፓርቲዎቹ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)፣ ህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ናቸው። 

የህብር ኢትዮጵያ ተወካይ ከመጀመሪያው ቀን በኋላ “በግል ምክንያት” ቆጠራውን አለመታዘባቸውን የጽህፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል። የቀሪ ሶስቱ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እና አምስት ምርጫ አስፈጻሚዎች ግን ቆጠራው እስከሚጠናቀቅ መገኘታቸውን አቶ ፍሬው አስረድተዋል።

በአማራ ክልል የደምቢያ 1 ምርጫ ክልል ለሚደረገው የድጋሚ ቆጠራ፤ ቆጠራውን የሚያከናውነው ቡድን ወደ ቦታው መንቀሳቀሱን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኳንንት መከተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም የድጋሚ ቆጠራውን በተመለከተ ወቅታዊ የሆነ መረጃ የለኝም ብለዋል።  

ለፓርላማ መቀመጫ ምርጫ ተደርጎበት ነገር ግን ምርጫ ቦርድ የድጋሚ ቆጠራ እንዲካሄድ ከወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች የመጨረሻው የሚገኘው በድሬዳዋ ከተማ ነው። ድሬዳዋ 2 ተብሎ በሚጠራው እና 101 ሺህ መራጮች በተመዘገቡበት በዚህ የምርጫ ክልል ቆጠራው ባለፈው ሳምንት አርብ መጀመሩን የምርጫ ቦርድ ድሬዳዋ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዚያድ ያሲን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምርጫ ክልል ካሉት 133 ምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ እስካሁን ቆጠራቸው የተጠናቀቀው የ62 ምርጫ ጣቢያዎች መሆኑን አቶ ዚያድ ጠቁመዋል። የምርጫ ክልሉን ቆጠራ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ከአራት እስከ አምስት ተጨማሪ ቀናት ሊወስድ እንደሚችልም ኃላፊው አስረድተዋል።

በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ መሰረት በድሬዳዋ 2 ምርጫ ክልል አንድ የግል ዕጩ እና ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የወከሉ ተወዳዳሪዎች ለተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ተፎካክረዋል። ፓርቲዎቹ እናት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ)፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ናቸው።

ድጋሚ እየተከናወነ ያለውን ቆጠራ እንዲታዘቡ ለሲቪክ ማህበራት እና በምርጫ ክልሉ ለተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ማቅረባቸውን የሚገልጹት አቶ ዚያድ፤ ሁለት የሲቪክ ማህበራት ቆጠራውን እየታዘቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ “እኛ ለሁሉም ጥሪ አቅርበናል። ከፖለቲካ ፓርቲዎችም የተገኙ አሉ” ብለዋል። ኃላፊው ተወካዮቻቸውን ያልላኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን ቢገልጹም በስም ከመጥቀስ ግን ተቆጥበዋል፡፡

የክልል ምክር ቤት ምርጫ አካሄደው የድጋሚ ቆጠራ እንዲከናወንባቸው የተወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች አጠቃላይ ብዛት ሰባት ሲሆን ከእነርሱ ውስጥ አምስቱ የሚገኙት በአፋር ክልል ነው። በክልሉ በሚገኙት በአምስቱም የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ድጋሚ ቆጠራ እስካሁን አለመጀመሩን የምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጠሃ አብዲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

“አንደኛው ላይ ለመጀመር አይመችም። ዞን አራት የሚባለው ቦታ ላይ ጦርነት አለ” ያሉት አቶ ጠሃ፤ በጉሊና ምርጫ ክልል አካባቢ ባለው ውጊያ ምክንያት የድጋሚ ቆጠራ ለማከናወን አለመቻሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

የአብአላ እና ኮነባ ምርጫ ክልሎች በሚገኙበት ዞን ሁለት ውጊያ ባይኖርም ስልክ ባለመስራቱ ምክንያት የድጋሚ ቆጠራውን ማከናወን እንዳልተቻለም የጽህፈት ቤት ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል። የአሚባራ ምርጫ ክልል ቆጠራ ከዛሬ ጀምሮ ሊከናወን ይችላል የሚሉት አቶ ጠሃ፤ የአብአላ እና ኮነባ ምርጫ ክልሎችን ቆጠራም ለማከናወን ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።  

የክልል ምክር ቤት ምርጫ ድጋሚ ቆጠራ እንዲደረግ ውሳኔ ከተላለፈባቸው መካከል አንዱ የሚገኘው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው። በክልሉ ሸርቆሌ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው በዚሁ የምርጫ ክልል ድጋሚ ቆጠራው መጠናቀቁን የምርጫ ቦርድ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ለማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ረፋድ ላይ ተጀመረው የድጋሚ ቆጠራ፤ ከአንድ ቀን በኋላ ባለፈው ቅዳሜ መጠናቀቁንም ኃላፊው ጨምረው ገልጸዋል። በምርጫ ክልል ደረጃ የተጠናቀቀው የቆጠራ ውጤትም በዛሬው ዕለት ወደ ማዕከል መላኩን ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)