ዩኒሴፍ በአፋር ክልል በተፈናቃዮች ላይ ተፈጸመ የተባለው ግድያ እንዳስደነገጠው ገለጸ

በሃሚድ አወል

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በአፋር ክልል በጤና ተቋም እና ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ከ100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ፤ 200 የሚልቁ ተፈናቃዮች ተገድለዋል መባሉ በእጅጉ እንዳስደነገጠው አስታወቀ። በአፋር እና በሌሎች የትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች የሚደረገው ውጊያ ተጠናክሮ መቀጠሉ ለህጻናት አስከፊ መሆኑንም ድርጅቱ ገልጿል።

ዩኒሴፍ በአፋር ክልል ተጠልለው በነበሩ ተፈናቃዮች ላይ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ በተመለከተ መግለጫ ያወጣው ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 3፤ 2013 ነው። በድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር ስም የወጣው ይኸው መግለጫ፤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የምግብ ዋስትና ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ አካባቢ፤ ወሳኝ የምግብ አቅርቦቶች ወድመዋል መባሉንም ጠቅሷል።

የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪታ ፎር | ፎቶ፦ ዩኒሴፍ

የተመድ የህጻናት መርጃ ድርጅት በአፋር ክልል ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት እና ስለ ደረሰው ጉዳት በመግለጫው ቢጠቅስም፤ ድርጊቱን የፈጸመው አካል የትኛው ወገን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥቧል። የአፋር ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባለፈው አርብ ሐምሌ 30 ባወጣው መግለጫ ለጥቃቱ የህወሓት ኃይሎችን ተጠያቂ አድርጎ ነበር።   

“የህወሓት ኃይሎች ከያሎ እና ጎሊና ወረዳዎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል፤ በጎሊና ወረዳ ጋሊኮማ የምትባል ቀበሌ በጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ተጠልለው የነበሩ አርብቶ አደሮች ላይ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት በመክፈት ጭፍጨፋ አካሂዷል” ሲል የክልሉ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ወንጅሏል። በጥቃቱም ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች የቀረበ አስቸኳይ የምግብ እና አልባሳት እርዳታ “ሙሉ በሙሉ” መውደሙን ማስታወቁ ይታወሳል። 

ዩኒሴፍ በዛሬው መግለጫው በአፋር እና በሌሎች የትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች የሚደረገው ውጊያ ተጠናክሮ መቀጠሉ “ለህጻናት አስከፊ ነው” ብሏል። በሰሜን ኢትዮጵያ ለወራት የዘለቀው ውጊያ 160 ሺህ ህጻናትን ጨምሮ 400 ሺህ ሰዎችን ወደ ረሃብ መሰል ሁኔታዎች እንዲገቡ አድርጓቸዋል ሲልም የሁኔታውን አሳሳቢነት ጠቁሟል። 

ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ክልልን ጨምሮ ውጊያው በተስፋፋባቸው አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች፤ አራት ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የሚባል የምግብ እጥረት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልጿል። “የምግብ ዋስትና ቀውሱ የተከሰተው ህጻናት እና ማህበረሰቦች የሚገለገሉባቸው የጤና ተቋማት ስልታዊ የሆነ ውድመት እየደረሰባቸው ባለበት ወቅት” መሆኑንም ድርጅቱ አስታውቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ በአካባቢው ባለው ውጊያ ሳቢያ መሆኑን የጠቆመው ዩኒሴፍ፤ ችግሩ ሊፈታ የሚችለውም “በውጊያው እየተሳተፉ ባሉት አካላት ብቻ ነው” ሲል አሳስቧል። ሁሉም አካላት ውጊያውን እንዲያቆሙ፣ የሰብዓዊ የተኩስ አቁምን በአፋጣኝ እንዲተገብሩ እንዲሁም የቻሉትን ሁሉ ነገር ተጠቅመው ህጻናትን ከጉዳት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)