ከታሰሩ 16 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች መካከል አስሩ ተፈቱ

በሃሚድ አወል 

በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ከታሰሩ 16 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች መካከል አስሩ ዛሬ ረፋድ ላይ በዋስ መፈታታቸውን በእስር ላይ የነበሩት ጋዜጠኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከእስረኞቹ መካከል የአስራ አራቱ ጠበቃ የሆኑት አቶ ታደለ ገብረመድህን አስር ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች መፈታታቸውን አረጋግጠው፤ ሆኖም አሁንም ያየሰው ሽመልስ፣ አበባ ባዩ፣ በቃሉ አላምረው እና ፋኑኤል ክንፉ የተባሉት የኢትዮ ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች በእስር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንድ የአውሎ ሚዲያ ሰራተኛ በእስር ላይ ከነበሩት 16 ጋዜጠኞች ውስጥ ስድስት ወንዶች እና አራት ሴቶች፤ በድምሩ አስር እስረኞች መፈታታቸውን እና ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ገደማ አዲስ አበባ መግባታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። ከእስር ከተፈቱት ውስጥ በአውሎ ሚዲያ በጋዜጠኝነት፣ በግራፊክስ ኤዲቲንግ ባለሙያነት እና በሰው ሃይል አስተዳደር ክፍል የሚሰሩት ፋና ነጋሽ፣ ምህረት ገብረክርስቶስ፣ ፍቅርተ የኑስ እና ዊንታና በርሄ የተባሉ ታሳሪዎች እንደሚገኙበት ለማረጋገጥ ተችሏል። 

እነዚህ አራት የአውሎ ሚዲያ ሰራተኞችን ጨምሮ ሰባት ተጠርጣሪዎች በዛሬው ዕለት በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀጠሮ የነበራቸው ቢሆንም፤ በችሎት ሳይቀርቡ ከምሳ ሰዓት በፊት ከእስር መለቀቃቸውን ከተፈቺዎቹ ጋዜጠኞች አንዷ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። “ዛሬ ቀጠሯችን ነበር፤ ግን አልቀረብንም። ፈቱን እና በራሳቸው መኪና ወደ አዲስ አበባ አመጡን” ስትል በደህንነት ስጋት ምክንያት ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀቸው ጋዜጠኛዋ አስረድታለች። 

የአስራ ስድስቱን ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞችን የምርምራ ጊዜ ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ በዛሬው የችሎት ውሎ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጉዳይ ለመመልከት ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል። ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል በነበሩት የችሎት ውሎዎች፤ የፌደራል ፖሊስ ለሶስት ጊዜ ያህል የጠየቃቸውን የምርምራ ጊዜዎች የፈቀደ ሲሆን፤ በዛሬው ቀጠሮው “የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ይቀበላል” ተብሎ ተጠብቆ ነበር።  

በእስር ላይ ከነበሩት ጋዜጠኞች ውስጥ ሌላኛዋ እስከሚፈቱበት ሰዓት ድረስ የሚያውቁት፤ ዛሬ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። “ባለፈው ቀጠሮ ‘የዋስትና ጥያቄያችሁን በጽሁፍ አቅርቡ’ በተባልነው መሰረት፤ የዋስትና ጥያቄያችንን እና የአያያዝ ጥያቄያችንን በዛሬው ቀጠሮ ለመስጠት ነበር ያሰብነው” የምትለው ጋዜጠኛዋ፤ “ፍርድ ቤት ከመሄዳችን በፊት ረፋድ አካባቢ መጡና፣ ከሴቶች ሁላችንንም ሴቶች፤ ከወንዶች ደግሞ መርጠው እንድንወጣ አደረጉን” ስትል ከእስር ስለተፈቱበት አካሄድ አብራርታለች።

የዛሬውን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለመከታተል ወደ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ያቀኑ የአንድ የጋዜጠኛ ቤተሰብ በበኩላቸው፤ አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት በደረሱበት ወቅት ጋዜጠኞቹ ከእስር ተፈተው ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸውን እዚያው ፍርድ ቤት እንደሰሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በሶስት መዝገብ ተከፍለው ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የነበሩት ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች፤ ምርመራ ስር የቆዩት “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ወንጀል ተጠርጥረው እንደሆነ ፖሊስ ገልጾ ነበር።  

በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ አበባ ባዩ እና ፋኑኤል ክንፉ የተባሉት የአውሎ ሚዲያ እና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች አሁንም በእስር ላይ መሆናቸውን ጠበቃቸው ገልጸዋል   

የኢትዮ ፎረም አዘጋጅ በሆነው በያየሰው ሽመልስ ምድብ ፍርድ ቤት ስትቀርብ የነበረች ጋዜጠኛ፤ ከመፈታታቸው በፊት በተሰጣቸው ወረቀት ላይ የራሳቸውን ስም እና ዋስ የሚሆናቸውን ግለሰብ ስም መጻፋቸውን ተናግራለች። መርማሪዎቹ “ ‘እኛ ወደ አዲስ አበባ ስንለመስ ትጠራላችሁ፤ ዋስ ታመጣላችሁ’ አሉን” ስትልም ዋስ የሚሆኗቸው ግለሰቦች አዲስ አበባ ፌደራል ፖሊስ ቢሮ ተገኝተው ይፈርማሉ መባሉን ገልጻለች። 

በተመሳሳይ መዝገብ ስር የነበረችው ሌላኛዋ ጋዜጠኛ በበኩሏ“[ፖሊሶቹ] በዋስ እየወጣን እንዳለንና ዋስ የሚሆኑንን ግለሰቦች እዚህ [አዋሽ ሰባት] መጥራት እንደከበዳቸው ገልጸው፤ እኛ ስማችንን መዝግበን እና ፈርመን እንድንወጣ አደረጉ” ስትል የአፈታታቸውን ሁኔታ አስረድታለች። ዋስ የሚሆኗቸውን ግለሰቦች ጉዳይ በተመለከተ “[ፖሊሶቹ] ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ዋሶቻችንን ፌደራል ፖሊስ ቢሮ እንድናቀርብ ነገሩን” ብላለች።  

የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በቃሉ አላምረው እና የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኛ አበባ ባዩ በተካተቱበት መዝገብ ስር የነበረው ጋዜጠኛም፤ የሁለቱን ተፈቺዎች ገለጻ አጠናክሯል። “እዚያ ስንፈልጋችሁ ማግኘት ስለምንችል በሚል ነው ወረቀት አስፈርመው የለቀቁን” ሲል ጋዜጠኛውን የተፈቱበትን አካሄድ በአጭሩ ገልጿል። 

ዛሬ የተፈቱት እና በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ “የፖሊሶች ማሰልጠኛ ካምፕ” ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ የቆዩት የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በፖሊስ የተያዙት ሰኔ 22፤ 2013 ነው። የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች የሆኑት አበበ ባዩ እና ያየሰው ሽመልስ ደግሞ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰኔ 24 እና 25 መሆኑን ጠበቃቸው አቶ ታደለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከዚህ ቀደም መግለጻቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)