በትግራይ ክልል የሚገኙ ሁለት የስደተኛ መጠለያዎች ለእርዳታ ሰራተኞች እንደገና ተደራሽ ሆነዋል ተባለ

በሃሚድ አወል 

በትግራይ ክልል የሚገኙት ማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ የተባሉት የኤርትራውያን ስደተኛ መጠለያዎች ለእርዳታ ሰራተኞች እንደገና ተደራሽ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቀ። ድርጅቱ ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ በሁለቱ የስደተኛ መጠለያዎች ለተጠለሉ 23 ሺህ ያህል ስደተኞች የሚያስፈልገውን አስቸኳይ እርዳታ ማቅረብ ጀምሬያለሁም ብሏል።

የUNHCR ቃል አቃባይ ቦሪስ ቼሺርኮቭ ዛሬ በስዊዘርላንድ ጄነቫ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ ሁለቱ የስደተኛ መጠለያዎች ባሉበት አካባቢ የነበረ “ኃይለኛ ግጭት” የድርጅቱን ሰራተኞች ከሐምሌ 6 ጀምሮ ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ እንዳይደርሱ አግዷቸው ቆይቷል። የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን እና አጋሮቹ ወደ ሁለቱ መጠለያዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ መድረስ ቢጀምሩም፤ በአካባቢው ያለው ውስብስብ እና ተለዋዋጭ የደህንነት ሁኔታ አሁንም ተደራሽነቱን የተገደበ እንዳደረገው ገልጸዋል። 

በዚህም ምክንያት ኤርትራውያን ስደተኞች አስከፊ ሁኔታዎችን መጋፈጥ መቀጠላቸውን ቃል አቃባዩ ጠቁመዋል። “እንደ ጤና እንክብካቤ ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች የሉም። ንጹህ የመጠጥ ውሃም እየተመናመነ ነው” ሲሉም የሁኔታውን አሳሳቢነት አስረድተዋል።  

ድርጅቱ በሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን አዲስ ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ ለማዘዋወርም ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንዲመቻችለት ጥሪ አቅርቧል። አዲስ የተዘጋጀው የአለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ በአማራ ክልል ዳባት ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ነው።  

ከማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ መጠለያዎች 135 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኘው የአለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ የተቋቋመው በተመድ የስደተኞች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ትብብር ነው። ወደ አዲሱ መጠለያ የተዘዋወሩ የመጀመሪያዎቹ 126 ስደተኞች ድጋፍ እያገኙ መሆኑን የUNHCR ቃል አቃባይ በዛሬው መግለጫቸው ጠቅሰዋል።   

UNHCR እና አጋሮቹ፤ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የነፍስ አድን ሰብዓዊ እርዳታ እና ጥበቃ ያቀርቡ ዘንድ፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በክልሉ ያልተገደበ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ቃል አቃባዩ አሳስበዋል። ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ ተደራሽነት መሻሻሎችን በማሳየቱ፤ የድርጅቱ ሰራተኞች እና አስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የያዙ 12 የጭነት ተሸከርካሪዎች በክልሉ ዋና ከተማ መቀሌ መድረሳቸውንም ቼሺርኮቭ አስታውሰዋል።  

ቃል አቃባዩ በዛሬው መግለጫቸው ያነሱት ሌላው ጉዳይ በአማራ እና አፋር ክልሎች ባለው ግጭት እየተከሰተ ያለው የሰዎች መፈናቀልን ነው። የአካባቢ ባለስልጣናትን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮን (OCHA) የጠቀሱት ቼሺርኮቭ፤ በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል በድምሩ 170 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ይህ ሁኔታም ድርጅታቸውን እንደሚያሳስበው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)