ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ ሲጓዙ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 7 ሰዎች ተገደሉ

በሃሚድ አወል

በአማራ ክልል ከምትገኘው ቻግኒ ከተማ ተነስተው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማ ወደ ሆነችው ግልገል በለስ ሲጓዙ በነበሩ ሁለት የህዝብ ማመላሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች ላይ በትላንትናው ዕለት በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን የሆስፒታል ምንጮች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ። የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ዋና አስተባባሪ የሆኑት ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ ጥቃቱ መፈጸሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

በተሽከርካሪዎቹ ላይ ጥቃቱ የተሰነዘረው በማንዱራ ወረዳ መግቢያ ገነተ ማሪያም ከተማ ጅግዳ ስላሴ አካባቢ ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 4፤ 2013 ከቀትር በኋላ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። በጥቃቱ የተገደሉ የሰባት ሰዎች አስክሬን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ወደ ፓዌ አጠቃላይ ሆስፒታል አስክሬን ክፍል መግባቱን አንድ የሆስፒታሉ ሰራተኛ  ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። 

በፓዌ ሆስፒታል በጤና ባለሙያነት የሚያገለግሉ ሌላ ግለሰብም፤ የሰባት ሰዎች አስክሬን ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱን መመልከታቸውን ገልጸዋል። በጥቃቱ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታሉ የመጣ ሰው አለመኖሩንም አክለዋል። የህክምና ባለሙያዎቹ ሟቾቹ ሰባት እንደሆኑ ቢናገሩም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ቁጥሩ ከዚህም በላይ እንደሆነ ይገልጻሉ። 

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የግልገል በለስ መናኸሪያ ሰራተኛ በጥቃቱ ከሁለቱ ሚኒባሶች በድምሩ እስከ አስር ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። በማንዱራ ወረዳ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ አንድ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው በጥቃቱ የሞቱት ስምንት ሰዎች ናቸው ይላሉ። በገነተ ማርያም ከተማ የሚኖሩ አንድ የግብርና ባለሙያም፤ በመንግስት ሰራተኛው በተጠቀሰው የሟቾች ቁጥር ይስማማሉ።    

ጥቃቱ መፈጸሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት ሌተናል ጄነራል አስራት ዴኔሮ፤ የደረሰውን የጉዳት መጠን በተመለከተ ግን “ዝርዝር መረጃ የለኝም” ብለዋል። ጥቃት ወደ ተፈጸመበት ቦታ “ክትትል ሊያደርግ የወጣ አጠቃላይ ሰራዊት አልተመለሰም” ሲሉም አክለዋል። ሌተናል ጄነራል አስራት “አደጋ ካደረሰው ኃይል ጋር ግጭቶች ነበሩ” ቢሉም፤ የጥቃት ፈጻሚዎቹን ማንነት ሳይገልጹ አልፈዋል።  

የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ጥቃቱን የፈጸሙት የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ከግልገል በለስ ማንዱራ ያለውን መንገድ ሲጠብቁ የነበሩ ታጣቂዎች ናቸው ባይ ናቸው። የግልገል በለስ መናኸሪያ ሰራተኛው “በመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት የተሃድሶ ስልጠና የወሰዱ የጉሙዝ ታጣቂዎች ናቸው ጥቃቱን የፈጸሙት” ሲል ይወነጅላል። ይህንን ገለጻ፤ የመንግስት ሰራተኛ እና የግብርና ባለሙያ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ አስተጋብተውታል።

ሁለቱ ነዋሪዎች፤ በታጣቂዎች ከተገደሉት በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም ታግተው መወሰዳቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የገነተ ማሪያም ነዋሪ የሆኑት የግብርና ባለሙያ፤ ወደ ህዳሴው ግድብ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ ከእነ ሹፌሩ በታጣቂዎች መታገቱን ገልጸዋል። 

ወደ ህዳሴው ግድብ ሲጓዙ የነበሩት “ፌሮ” ብረት የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች እንደሆኑ የጠቆመው የግልገል በለስ መናኸሪያ ሰራተኛው፤ መኪናዎቹ የፊት ጎማቸው ተመትቶ ቆመዋል ብሏል። በማንዱራ ወረዳ የመንግስት ሰራተኛው ደግሞ ወደ ህዳሴው ግድብ ከሚሄዱ ተሽከርካሪዎች በተጨማሪ የህዝብ ማመላሻ ተሽከርካሪዎች እና የጭነት መኪናዎች በአካባቢው መታገታቸውን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)