በሃሚድ አወል
የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በእስር ላይ በሚገኙ ሶስት ጋዜጠኞች ላይ ለአራተኛ ጊዜ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ የምርመራ ጊዜውን የፈቀደው የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ በሆነው በቃሉ አላምረው፣ በሚዲያው ላይ በተንታኝነት በሚሳተፈው ፋኑኤል ክንፉ እንዲሁም የ“ኢትዮ ፎረም” ጋዜጠኛ በሆነው አበበ ባዩ ላይ ነው።
የወረዳው ፍርድ ቤት ለዛሬ ነሐሴ 6፤ 2013 ቀጥሮ የነበረው፤ ፖሊስ ባለፈው ችሎት በተፈቀደለት አስር የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለመስማት ነበር። ነገር ግን ፖሊስ “ምርመራዬን አላጠናቀቅኩም” በማለቱ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ አራት የምርመራ ቀናት መፍቀዱን የጋዜጠኞቹ ጠበቃ አቶ ታደለ ገብረመድሀን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዛሬው የችሎት ውሎ ከሶስቱ ጋዜጠኞች ጋር አብሮ ፍርድ ቤት በቀረበው አክቲቪስት ጸጋዘአብ ኪዳኔ ላይም፤ ፖሊስ ተመሳሳይ የምርመራ ቀናት እንደተፈቀደለት ጠበቃው አስረድተዋል። አራቱም ተጠርጣሪዎች በዛሬው ችሎት ለፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄ ቢያቀርቡም ውድቅ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።
ፖሊስ ሶስቱን ጋዜጠኞችን እና አክቲቪስቱን ጨምሮ በቁጥጥር ስር አውሏቸው የነበሩ 16 ግለሰቦችን “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ወንጀል መጠረጠሩን ከዚህ ቀደም ማስታወቁ አይዘነጋም። ከአስራ ስድስቱ ተጠርጣሪዎች መካከል አስሩ ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 3፤ 2013 ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል።
አሁንም በእስር ላይ ከሚገኙት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው የ“ኢትዮ ፎረም” አዘጋጅ ያየሰው ሽመልስ፤ ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርቦ ለመጪው ሰኞ ነሐሴ 10 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል። ጋዜጠኛው በዕለቱ በነበረው የችሎት ውሎ፤ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱን እንዲያከብርለት በጽሁፍ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ጠበቃው አቶ ታደለ ገብረመድሀን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ፍርድ ቤቱ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቅድለት መጠየቁንም ጠበቃው ጠቁመዋል። የሁለቱንም ጥያቄዎች ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ጋዜጠኛ ያየሰው ባቀረበው የዋስትና ጥያቄ ላይ ፖሊስ አስተያየት እንዲሰጥ እና የተጠየቀውን የምርመራ ጊዜን ተመልክቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ለነሐሴ 10፤ 2013 ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃው ጨምረው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)