የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አድርገው የሾሟቸው ጄፍሪ ፌልትማን፤ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ልዩ  መልዕክተኛው ከነገ በስቲያ እሁድ ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደሚጓዙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። 

በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቃባይ ቢሮ ሐሙስ ለሊት በወጣው መግለጫ መሰረት፤ ፌልትማን በሶስቱ ሀገራት ለ10 ቀናት ያህል ቆይታ ያደርጋሉ። ልዩ መልዕክተኛው በቆይታቸው፤ ከሶስቱ ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ በመግለጫው ተጠቅሷል። ውይይቱ፤ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ “ሰላምን የምታበረታታባቸው” እና የቀጠናውን “መረጋጋት እና ብልጽግና የምትደግፈባቸውን” ዕድሎች የተመለከተ እንደሚሆን ተገልጿል።

የፕሬዝዳንት ባይደን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ከዚህ መግለጫ መውጣት ሰዓታት አስቀድሞ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ልዩ መልዕክተኛው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ ጥቆማ ሰጥተው ነበር። የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው በዚሁ መልዕክታቸው፤ “በዚህ ወሳኝ ወቅት፤ ፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል” ብለዋል።

“ለወራት የዘለቀው ጦርነት በታላቋ ሀገር ላይ ከፍተኛ ስቃይ እና ክፍፍል አምጥቷል። ይህ ሁኔታ በተጨማሪ ውጊያ አይሽርም” ያሉት ሱሊቫን፤ ሁሉም ወገኖች “ወደ ድርድር ጠረጴዛ በአስቸኳይ እንዲመጡ” ጥሪ አቅርበዋል። ይህንን የአማካሪውን መልዕክት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወርም በትዊተር ገጻቸው አስተጋብተውታል።  

መልዕክቱን “አስቸኳይ” ሲሉ የጠሩት ሳማንታ ፓወር፤ “ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትሔ የለም” ሲሉ በትግራይ ያለው ቀውስ ሊፈታ የሚችለው በድርድር መሆኑን ገልጸዋል። “የሰብዓዊ ፍላጎቶች አንገብጋቢ ሆነዋል። ሁሉም ወገኖች ለድርድር ተስማምተው ውጊያዎችን ካላቆሙ ግን ከዚህም በላይ የከፋ ይሆናሉ” ብለዋል።   

ባለፈው ግንቦት መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ አቅንተው የነበሩት ፌልትማን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል። አሜሪካ፤ የትግራይ ግጭትን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አሳሳቢ ላለቻቸው ችግሮች መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ፌልትማንን በልዩ መልዕክተኛነት የሾመቻቸው ባለፈው ሚያዝያ ወር ነበር። 

ልዩ መልዕክተኛው ሹመታቸውን ተከትሎ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዞ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ኤርትራ፣ ግብጽ እና ሱዳን አቀንተው ከሀገራቱ መሪዎች ጋር መክረዋል። የህዳሴው ግድብ ውዝግብን ጨምሮ ለሌሎችም የአፍሪካ ቀንድ ቀውሶች መፍትሔ ለማምጣት ባለመው ሁለተኛ ጉዟቸው ደግሞ፤ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኬንያን አካልለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[* በዚህ ዘገባ ቀደምት ክፍል ላይ ጄፍሪ ፌልትማን ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ ሶስት ሀገራት የሚጓዙት ከቅዳሜ ጀምሮ መሆኑ ተጠቅሶ ነበር።  ዘግየት ብሎ “ከእሁድ ጀምሮ” በሚለው ተስተካክሏል]