በትግራይ ክልል ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎችን የማስመለስ ሂደት ተጠናቀቀ

– በወልዲያ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ የትግራይ ክልል ተማሪዎችም ዛሬ ወደ መቐለ ተሸኝተዋል 

በበእምነት ወንድወሰን

በትግራይ ክልል ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎችን የማስመለስ ሂደት መጠናቀቁን ተማሪዎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ አስታወቀ። በራያ ዩኒቨርስቲ የነበሩ ተማሪዎች ትላንት ተጠቃልለው ወደ አፋር ክልል የገቡ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ በወልዲያ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ የነበሩ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ወደ መቐለ ተሸኝተዋል። 

የቴክኒካል ኮሚቴ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አባተ ጌታሁን፤ ኮሚቴው በትግራይ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን የማስመለስ ሂደቱን ትናንት ማምሻውን ሙሉ ለሙሉ መጨረሱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ አባላት ያሉበት ይኸው ኮሚቴ፤ ሂደቱን በቅርበት ሆኖ ለማስፈጸም የአፋር ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነችው ሰመራ የገባው ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ነበር። 

በስፍራው ከአንድ ወር በላይ ቆይታ ያደረገው ኮሚቴው፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎችን የተቀበለው ከሶስት ሳምንት በፊት ሐምሌ 18 ነበር። ኮሚቴው በመቐለ ዩኒቨርስቲ ይማሩ ለነበሩ ተማሪዎች ቅድሚያውን የሰጠ ሲሆን፤ በማስከተልም በአክሱም እና አዲግራት ዩኒቨርስቲዎች የነበሩ ተማሪዎች ከትግራይ ክልል እንዲመለሱ አድርጓል። 

በትግራይ ክልል ስር ያለው ራያ ዩኒቨርሲቲ፤ በቴክኒካል ኮሚቴው “የመጀመሪያ እቅድ ውስጥ አልነበረም” የሚሉት ዶ/ር አባተ፤ የትግራይ አማጽያን አካባቢያውን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ ያለው የተማሪዎች አስመላሽ አብይ ኮሚቴ ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲው  የማውጣት ውሳኔ ላይ መድረሱን አብራርተዋል። የቴክኒካል ኮሚቴው በዩኒቨርስቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎችን በዚህ ሳምንት ለማስመለስ 34 አውቶብሶችን አዘጋጅቶ ሲጠባበቅ መቆየቱን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አስታውቀዋል። 

በዚህም መሰረት በትላንትናው ዕለት 1,149 የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እና መምህራን በ20 አውቶብሶች ተሳፍረው በአፋር ክልል ሰመራ ዩኒቨርስቲ መድረሳቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል። ተማሪዎችን ሊያጓጓዙ ከሄዱ አውቶብሶች ውስጥ አስራ አራቱ ባዷቸውን መመለሳቸውንም አክለዋል።

የአፋር ክልልን ከትግራይ ጋር በምታዋስነው አብኣላ ከተማ የሚኖሩ አምስት ነዋሪዎች፤ ተማሪዎችን የጫኑ ከ15 በላይ የሚሆኑ አውቶብሶች ትላናት ከሰዓት ከተማዋን ሲያቋርጡ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ማምሻውን ደግሞ ሰዎችን ያልጫኑ 6 አውቶብሶች ተከታትለው ሲጓዙ መመልከታቸውንም አስረድተዋል። በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የአይን እማኞች በበኩላቸው ተማሪዎችን የጫኑ 20 የሚሆኑ አውቶብሶች ሰመራ ዩኒቨርሲቲ የደረሱት ትናንት ማምሻውን “12 ሰዓት ገደማ ነው” ብለዋል።

የራያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን የጫኑ አውቶብሶች ዛሬ ጠዋት ከሰመራ ዩኒቨርስቲ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀምረዋል | ፎቶዎች፦ ቲክቫህ ዩኒቨርስቲ

የራያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ትላንት ሐሙስ በአብኣላ ከተማ ተገኝተው የተቀበሉት የተማሪዎች አስመላሽ ቴክኒካል ኮሚቴ አባላቱ፤ ዛሬ ረፋዱን ደግሞ ከወልዲያ እና ከወሎ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎችን ሲሸኙ ማርፈዳቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል። እያንዳንዳቸው 30 ተማሪዎችን በያዙ ሶስት አውቶብሶች ተማሪዎቹ መሸኘታቸውንም ጠቁመዋል። 

በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 202 የሚሆኑ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ሐምሌ 21 ከዩኒቨርሲቲው ይወጣሉ ተብሎ አስቀድሞ ቢገለጽም፤ ዩኒቨርስቲውን ለቅቀው ወደ ሰመራ ዩኒቨርስቲ የተጓዙት ግን ከሳምንት በኋላ እንደነበር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘደንት ዶ/ር አበበ ግርማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡

“በወቅቱ ከወልዲያ ወደ አፋር መሄጃ መንገዶች ላይ ጦርነት እያንዣበበ ነበር። ስለዚህም ተማሪዎቹን ይዘን ስንጓዝ ከለላ ያስፈልገን ነበር። እሱን ከለላ አላገኘንም ነበር። ስለዚህ ተማሪዎቹን አልሸኘናቸውም ነበር” ሲሉ ዶ/ር አበበ ተማሪዎቹ በተባለው ቀን ያልወጡበትን ምክንያት አስረድተዋል። “ሐምሌ 28 ግን እኔው እራሴ ተማሪዎቹን ይዤ፤ ከወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በፌደራል ፖሊስ ኃይል ታጅበን፤ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ለሚገኘው ተማሪዎችን ከትግራይ ክልል ተቀብሎ ለሚሸኘው ቴክኒካል ኮሚቴ ክፍል አስረክቤያለሁ” ሲሉ የተማሪዎቹን የሽኝት ሂደት አብራርተዋል።

በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 202 የሚሆኑ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ሐምሌ 21 ከዩኒቨርሲቲው ይወጣሉ ተብሎ አስቀድሞ ቢገለጽም፤ በአካባቢው ባለው ውጊያ ምክንያት ዩኒቨርስቲውን ለቅቀው ወደ ሰመራ ዩኒቨርስቲ የተጓዙት ከሳምንት በኋላ ነው | ፎቶ ፋይል፦ ወልዲያ ዩኒቨርስቲ

በትግራይ ክልል የሚገኙ ተማሪዎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ፤ አንድ ወር ገደማ በፈጀ ሂደት ማስመለስ የቻላቸው ተማሪዎች 10,164 እንደሆኑ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ አርብ ነሐሴ 7 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከተማሪዎቹ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከመቐለ ዩኒቨርስቲ የመጡ ሲሆን ብዛታቸው 3,668 ነው። የአክሱም ዩኒቨርስቲ 2,992 ተማሪዎች በብዛት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ከአዲግራት ዩኒቨርስቲ የተመለሱት ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ 2,355 መሆናቸውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ ያመለክታል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው፤ በትግራይ ክልል መቐለ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ሰባት ተማሪዎች በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ “ምንም ዓይነት አካላዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ጥቃት እንዳልደረሰባቸው” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የመከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቅቆ ከወጣ በኋላ፤ ከዩኒቨርሲቲው እስከወጡበት እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት ድረስም ሰላማዊ ቆይታ እንደነበራቸው ገልጸዋል። 

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተመላሽ ተማሪዎች በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል የወጣ ዕለት የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሰዎች ደስታቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጻቸውን አስታውሰዋል። ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጋር የስልክ ቆይታ የነበራቸው አምስት የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው በነበሩት ጊዜ ስጋት እንዳልነበረባቸው አስረድተዋል።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አምስት የአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወደ አፋር እስከገቡበት ቀን ድረስ ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው ተናግረዋል። | ፎቶ ፋይል፦ አክሱም ዩኒቨርስቲ

በዩኒቨርስቲው ስለነበራቸው ቆይታ የተጠየቁት አምስት የአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም፤ የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች ትግራይን ለቅቆ በወጣበት ሰኔ 21 ምሽት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ደመቅ ያለ ደስታን የመግለጽ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከወትሮው የተለየ ግርግር እንደነበረ ተናግረዋል። በዚያን ዕለት በነበረ ግርግር “ላፕ ቶፕ” እና “የሞባይል ስልኮች የተሰረቁባቸው ተማሪዎች መኖራቸውን ሰምተናል” ብለዋል ።

የዩኒቨርስቲው የሶስተኛ ዓመት ተማሪ “ጉዳዩን ድንገት ስለሰማን ተደናግጠን ነበር። ስጋትም ስለነበረን ችግር የተፈጠረ መስሎን ነበር። ከዩኒቨርሲቲው ለማምለጥ የሞከሩ ተማሪዎችም ነበሩ። ነገሩን ካወቅን በኋላ ግን ተረጋጋን” ሲል በወቅቱ የነበረውን ስሜት ይገልጻል። አምስቱም የአክሱም ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወደ አፋር እስከገቡበት ቀን ድረስ ምንም ችግር እንዳልገጠማቸው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)