በደቡብ ክልል ሰገን ወረዳ በደረሰ ጥቃት ሶስት ሰዎች ተገደሉ

በበእምነት ወንድወሰን 

በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን ስር በምትገኘው ሰገን ከተማ ታጣቂዎች ትናንት ምሽት በከፈቱት ተኩስ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ አራት ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው የአካባቢው ባለስልጣናት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት ታጣቂዎቹ ቦምብ ጭምር በመወርወር ጉዳት ማድረሳቸውንም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

የትላንቱ ጥቃት የተሰነዘረው በሰገን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አካባቢ ባለ አንድ አነስተኛ ምግብ ቤት ውስጥ በመመገብ ላይ ባሉ ሰዎች መሆኑን የሰገን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ከተማ ዴሌቦ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ትናንት እሁድ ነሐሴ 9፤ 2013 ምሽት ከሁለት ሰዓት በኋላ በደረሰው በዚህ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ማለፉንም ጨምረው አስረድተዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉት ግለሰቦች መካከል አንደኛው በሰገን ሆስፒታል በነርስነት የሚያገለግል ባለሙያ እንደነበር የኮንሶ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰራዊት ቲቶ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የህክምና ባለሙያው የተገደለው፤ ከጓደኞቹ ጋር በሆስፒታሉ አቅራቢያ በሚገኝ አነስተኛ ምግብ ቤት እራት በመመገብ ላይ ባለበት ወቅት ነው ብለዋል። የሰገን ወረዳ አስተዳዳሪ በበኩላቸው በምግብ ቤቱ ውስጥ የነበረው ግለሰብ የተገደለው በታጣቂዎች በተወረወረ ቦምብ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሰራዊት ገለጻ፤ ታጣቂዎቹ በከፈቱት ተኩስ በምግብ ቤቱ አጠገብ በሚገኝ መኖሪያ ቤት የነበሩ የባል እና ሚስት ህይወትም በተጨማሪነት ቀጥፏል። በጥቃቱ የቆሰሉ አምስት ሰዎች በአሁኑ ሰዓት በሰገን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህክምና እየተረዱ መሆናቸውን የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል። 

በኮንሶ ዞን ሰገን ዙሪያ ወረዳ እንዲህ አይነቱ ጥቃት ሲደርስ የአሁኑ መጀመሪያ አይደለም። በዚህ ዓመት ህዳር ወር መጨረሻ ላይ በወረዳው ዙሪያ በደረሰ ጥቃት የ66 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 39 ሰዎች መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጾ ነበር። በዚሁ ጥቃት ምክንያት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውንም ኮሚሽኑ በወቅቱ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።  

በኮንሶ ዞን ሰገን ወረዳ በንጹሃን ዜጎች ላይ ከአምስት ጊዜ በላይ ከፍተኛ ጥቃቶች መድረሳቸውን የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊም ይናገራሉ። በሰገን ከተማ ጥቃት የሚደርሰው ከግለሰቦች ባለፈም በመንግስት መስሪያ ቤቶችም ጭምር ላይ መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ሰራዊት፤ ጥቃቱ የሚሰነዘረው “ምሽት እና ጨለማን ተገን በማድረግ” ነው ብለዋል።    

በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩት እነዚህ ጥቃቶች “በኮንሶ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ” መሆናቸውን የሚገልጹት ኃላፊው፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም “የሽፍታ ባህሪ ያላቸው እና ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ የሚሰወሩ” እንደሆኑ ጠቁመዋል። ጥቃቱ መፈጸም የጀመረው “ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን” እየተባለ ይጠራ የነበረው አካባቢ በአዋጅ ፈርሶ፤ በኮንሶ ዞን ስር በሰገን ዙሪያ ወረዳ ስር እንዲጠቃለል ከተደረገ በኋላ መሆኑንም ያብራራሉ። 

ከዚህ ቀደም የነበረውን ጥቃት የሚያደርሱት “አካባቢው ላይ የመጣውን አዲስ የአስተዳደር ስርዓት የማይቀበሉ እና የ “‘ልዩ ወረዳ መዋቅር ጠያቂ ነን’ በማለት ራሳቸውን የሚጠሩ ኃይሎች ናቸው” ይላሉ አቶ ሰራዊት። የትላንትናውን ጥቃት የፈጸሙት ታጣቂዎች ማንነት አለመታወቁን የሚናገሩት የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ፤ “በመንግስት ክትትል እየተደረገባቸው ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የኮንሶ ዞን አስተዳደር ትላንት ምሽት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው የሀዘን መግለጫ፤ እነዚህን ጥቃቶች የሚያደርሰው ኃይል “በሰገን ከተማ ዙሪያ የከተመ ነው” ብሏል። “ጸረ ሰላም ኃይሎች” ከዚህ በኋላ ለሚያደርሱት ጥቃት ግን “መንግስት ትእግስት የለውም” ሲል አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[ እርማት፦ “ታጣቂዎች የወረወሩት ቦምብ ቢፈነዳም ጉዳት አላደረሰም” በሚል በዚህ ዘገባ ላይ ቀደም ሲል የተካተተው መረጃ ላይ እርማት መደረጉን ለመግለጽ እንወዳለን። መረጃ በማሰባሰብ ወቅት ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን]