በሃሚድ አወል
በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በእስር ላይ የሚገኙ አራት ጋዜጠኞችን የጊዜ ቀጠሮ ጉዳይ የሚመለከተው የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ እያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች አምስት ሺህ ብር ዋስትና አስይዘው እንዲፈቱ ዛሬ ውሳኔ መስጠቱን ጠበቃቸው እና ቤተሰቦቻቸው ገለጹ። ዛሬ ረፋዱን በዋስትና እንዲፈቱ ውሳኔ የተላለፈላቸው ጋዜጠኞች ያየሰው ሽመልስ፣ አበበ ባዩ፣ በቃሉ አላምረው እና ፋኑኤል ክንፉ ናቸው።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች የዋስትና ገንዘቡን ዛሬውኑ ከፍለው ቢጨርሱም፤ ተጠርጣሪዎቹ ሳይፈቱ መቅረታቸውን አስታውቀዋል። የዋስትና ክፍያ መፈጸሙን የሚያመለክተውን ሰነድ እና የፍርድ ቤቱን የትዕዛዝ ደብዳቤ በመያዝ 10 ሰዓት 45 ከደቂቃ ላይ አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ቢሮ የሄዱ የጋዜጠኞቹ ቤተሰቦች፤ “አሁን መሽቷል፤ ጠዋት ይፈታሉ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

በዛሬው ችሎት የ“ኢትዮ ፎረም” አዘጋጁ ያየሰው ሽመልስ እና ባልደረባው አበበ ባዩ፣ የአውሎ ሚዲያ ዋና አዘጋጅ የሆነው በቃሉ አላምረው እንዲሁም በሚዲያው በተንታኝነት የሚሳተፈው የቀድሞው የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ፋኑኤል ክንፉ በአካል ተገኝተዋል ተብሏል። በእነ በቃሉ አላምረው መዝገብ የተካተተው የአክቲቪስት ጸጋዘአብ ኪዳኔ ጉዳይን የተመለከተው ችሎቱ፤ ለእርሱም በተመሳሳይ የአምስት ሺህ ብር ዋስትና መፍቀዱን በቦታው የነበሩ ቤተሰቦች ገልጸዋል።
የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 6፤ 2013 በነበረው የችሎት ውሎ፤ በእነ በቃሉ መዝገብ የተካተቱ አራት ተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ እንዳደረገ ይታወሳል። ከአራቱ ተጠርጣሪዎች ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ፍርድ ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ተመሳሳይ የዋስትና ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ ችሎቱ ጉዳዩን ለመመልከት እና የፖሊስን አስተያየት ለማድመጥ ለዛሬ ቀጥሮ ነበር።
የፌደራል ፖሊስ አራቱን ጋዜጠኞችን እና አክቲቪስቱን ጨምሮ 16 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ያዋለው “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል ነበር። ከአንድ ወር በላይ በእስር ከቆዩት ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ሰራተኞች መካከል አስሩ፤ ባለፈው ነሐሴ 3፤ 2013 ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)