ምርጫ ቦርድ በጷጉሜ መጀመሪያ ሊያካሄድ የነበረውን ምርጫ ሊያራዝም ነው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ጷጉሜ 1 ሊያካሄደው የነበረውን ምርጫ ለማራዘም የሚያስችል አዲስ የጊዜ ሰሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቀረበ። ቦርዱ አዲሱ የድምጽ መስጫ ቀን መስከረም 18 እንዲሆን ምክረ ሃሳብ አቅርቧል ተብሏል። 

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ሰኔ 14 ምርጫ ሊደረግባቸው በማይቻልባቸው ቦታዎች፤ ጷጉሜ 1  ምርጫ እንዲካሄድ የወሰነው ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። የጸጥታ ችግር፣ የመራጮች ምዝገባ በአግባቡ አለመከናወን፣ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ ያጋጠሙ እንከኖች እንዲሁም ቦርዱ ምርጫውን በተመለከተ በፍርድ ቤት የነበሩበት ሙግቶች ለድምጽ አሰጣጡ ወደ ጷጉሜ እንዲዘዋወር የተደረገባቸው ምክንያቶች ነበሩ። 

ምርጫ ቦርድ ዛሬ ሐሙስ ነሐሴ 13 ከፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ስብሰባ ላይም፤ የጸጥታ ችግር ምርጫውን በድጋሚ ለማራዘም በምክንያትነት መቅረቡን በስብሰባው ላይ የተገኙ የተገኙ አንድ የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቦርዱ የጊዜ እጥረትን በተጨማሪ ምክንያትነት በስብሰባው ላይ ማንሳቱንም ገልጸዋል።

የዛሬውን ስብሰባ የተካፈሉ አንድ የሀገር አቀፍ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ በጸጥታ ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች በሌሉባቸው የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ቦርዱ መወሰኑን አስታውቀዋል። ምርጫ ሊካሄድባቸው እንደሚቻል በተገለጸባቸው የሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ድሬዳዋ እና ደቡብ ክልሎች ግን የድምጽ አሰጣጡን በመስከረም 18 ለማድረግ ቦርዱ ማቀዱን ገልጸዋል።  

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሁለቱ የፖለቲካ አመራሮች፤ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች “በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ” ምክንያት በምርጫው መራዘም ላይ ስምምነታቸውን ገልጸዋል ብለዋል። በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ “ምርጫውን መስከረም 18 ማካሄድ አግባብ አይደለም” የሚል ሃሳብ ጭምር ከፖለቲካ ፓርቲዎች መነሳቱንም አስረድተዋል። 

ይህን ሀሳብ ያነሱ ወገኖች፤ መስከረም ላይ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የፓርላማ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ መኖሩን በመከራከሪያነት ማንሳታቸውን ስብሰባውን የተከታተሉት የሀገር አቀፍ ፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ተናግረዋል። ምርጫ ባልተከናወነባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ምርጫ፤ “ሀገር በምትረጋጋበት ወቅት መካሄድ አለበት” የሚል ሃሳብ መንጸባረቁንም አብራርተዋል። 

የክልላዊ ፓርቲ አመራር የሆኑት ግለሰብ ምርጫውን በተባለው ጊዜ ለማካሄድ ያለውን አጭር ጊዜ በተመለከተ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከጷጉሜ 1 በፊት ያሉት ቀሪ የሁለት ሳምንት ጊዜያት የምርጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት፣ የምርጫ ቁሳቁስ ለመጓጓዝ፣ ለምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና ለመስጠት እና የመራጮች ምዝገባ ለማከናወን “በቂ አይደሉም” መባሉንም ጠቅሰዋል።   

ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ባሰራጨው ጊዜያዊ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ፤ መስከረም 18 ድምጽ የሚሰጥበት ቀን እንዲሆን ምክረ ሃሳብ ማቅረቡን በዛሬው ስብሰባ የተሳተፉ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “አሁን ባለው የጸጥታ ችግር መስከረም 18 ምርጫ እንዴት ማካሄድ ይቻላል?” የሚል ጥያቄ ከስብሰባው ተሳታፊዎች ተሰንዝሯል ተብሏል። ቦርዱ ምርጫው የሚከናወንበትን ትክከለኛ ቀን “በአጭር ቀናት ውስጥ አሳውቃለሁ” የሚል ምላሽ መስጠቱም ተገልጿል። 

የጷጉሜ 1 ምርጫን መራዘመን እና በዛሬው ስብሰባ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄዎች ብናቀርብም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)