የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ላይ ለ8ኛ ጊዜ ሊመክር ነው

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ በመጪው ሐሙስ በዝግ ሊመክር ነው። ምክር ቤቱ በትግራይ ክልል ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በጉዳዩ ላይ ሲወያይ የሐሙሱ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።

የትግራይ ሁኔታን በተመለከተ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንዲያደርግ የጠየቁት ስድስት ሀገራት መሆናቸውን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየርላንድ ተልዕኮ ከቀናት በፊት በትዊተር ገጹ ባወጣው መረጃ አስታውቆ ነበር። ይህን የስብሰባ ጥሪ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 13 በጋራ ያቀረቡት አየርላንድ፣ ኢስቶኒያ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ፣ ብሪታኒያ እና አሜሪካ መሆናቸውን ተልዕኮው ጠቁሟል።  

ስድስቱ ሀገራት ስብሰባው እንዲካሄድ የጠየቁት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው። የተመድ ዋና ጸሀፊ ጥሪውን ያቀረቡት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታስቦ የዋለውን የዓለም የሰብዓዊነት ቀንን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ ነው። 

ጉተሬዝ በዚሁ መግለጫቸው ስለ አፍጋኒስታን እና ሃይቲ ወቅታዊ ችግር ቢያነሱም፤ ይበልጡኑ ትኩረት ሰጥተው በዝርዝር የተናገሩት ግን በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ነው። ዋና ጸሀፊው በኢትዮጵያ ያልተገደበ የሰብዓዊ እንቅስቃሴ እንዲፈቀድ እና የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶችም ወደ ስራ እንዲመለሱም ጠይቀዋል። 

ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላለው ቀውስ መፍትሔ ማበጀት የሚያስችል፤ በኢትዮጵያውያን የሚመራ ፖለቲካዊ ውይይት መኖር እንዳለበት ጠቁመዋል። ይህንን ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ሁኔታዎች መመቻቸት እንዳለባቸውም አሳስበዋል። እነዚህን የዋና ጸሀፊውን ጥሪዎች፤ የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያን በተመለከተ ስብሰባ እንዲያካሄድ የጠየቁ ስድስት ሀገራት እንደሚደግፉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየርላንድ ተልዕኮ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ “ክፉኛ እንደሚያሳስባቸው” በተለያየ ጊዜ ባወጧቸው መግለጫቸው ሲያስታውቁ የሰነበቱት አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ በሐሙሱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የዲፕሎማቲክ ምንጮች ተናግረዋል። ከእርሳቸው በተጨማሪ በቅርቡ ኢትዮጵያ ደርሰው የተመለሱት የተመድ የሰብዓዊ እና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ በስብሰባው ላይ እንደሚሳተፉ እነኚሁ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ገልጸዋል። 

በሐሙሱ ስብሰባ ለጸጥታው ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑት የተመድ የሰብዓዊ እና የአስቸኳይ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትዝ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት ወደ ትግራይ ተጉዘው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በአካል ተመልክተዋል | ፎቶ፦ UN OCHA

በስብሰባው የሚጋበዙ፣ ከጸጥታው ምክር ቤት አባላት ውጭ ያሉ ባለስልጣናት የሚያቀርቡት ማብራሪያ በግልጽ የሚደመጥ መሆኑን ለሐሙስ የተያዘው የምክር ቤቱ አጀንዳ ያሳያል። የምክር ቤቱ አባላት ከዚያ በኋላ የሚያደርጉት ምክክር በዝግ የሚካሄድ እንደሚሆንም በአጀንዳው ላይ ተቀምጧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አስራ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን ከእነርሱ ውስጥ አምስቱ ቋሚ ናቸው። ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ቋሚ ሀገራት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ፈረንሳይ እና ብሪታንያ ናቸው። በየሁለት ዓመቱ ከሚቀያየሩት 10 ተለዋጭ አባላት መካከል፤ የኢትዮጵያን ጉዳይ አጥብቃ የያዘችው አየርላንድ፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ በተጠሩ ስብሰባዎች ስሟ ተደጋግሞ የሚነሳው ኢስቶኒያ እና የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ ይገኙበታል። 

በጸጥታው ምክር ቤት በየሁለት ዓመቱ ከሚቀያየሩት 10 ተለዋጭ አባላት መካከል አንዷ የሆነችው አየርላንድ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢትዮጵያን ጉዳይ አጥብቃ በመያዝ ጎልታ ታይታለች
ፎቶ፦ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየርላንድ ተልዕኮ

በተባበሩት መንግስታት ቻርተር አማካኝነት የዓለምን ሰላም እና ጸጥታ የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ የተወያየው ባለፈው ሰኔ 25፤ 2013 ነበር። በአየርላንድ፣ አሜሪካ እና ብሪታኒያ ጥያቄ መሠረት በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ተጋብዘው ተገኝተዋል።   

በሰኔው ስብሰባ፤ የተመድ የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝሜሪ ዲካርሎ እንዲሁም በወቅቱ የድርጅቱ የሰብዓዊ እና የአስቸኳይ እርዳታ ጊዜያዊ አስተባባሪ ሆነው ይሰሩ የነበሩት ራሜሽ ራንጃሲንገም ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል። በግልጽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ማብራሪያ ያቀረቡ የተመድ ኃላፊዎችም ሆነ የምክር ቤቱ አባላት፤ በትግራይ የነበረውን ወቅታዊ የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ስጋታቸውን መግለጻቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)