የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ያሳሰባቸው 60 የሚጠጉ የአፍሪካ ልሂቃን፤ የአፍሪካ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በሀገሪቱ ውጊያ የገጠሙ ኃይሎችን የማሸማገል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠየቁ። የዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ደራሲዎች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የተካተቱበት የልሂቃኑ ስብስብ ጥያቄውን ያቀረበው፤ ትላንት ሐሙስ ለሊት ይፋ በተደረገ ግልጽ ደብዳቤ ነው።
ደብዳቤውን ከፈረሙ ምሁራን መካከል የካናዳው ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማርታ ኩዌ ኩምሳ፣ የአሜሪካው ፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳግማዊ ውብሸት፣ የካሊፎርኒያው ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አወት ወልደሚካኤል ይገኙበታል። እንደ ካሜሮናዊው ፈላስፋ፣ የፖለቲካ “ቲዮሪስት” እና የአደባባይ ምሁር አቺሌ ሜምቤ እና ሴኔጋላዊው ደራሲ እና ጋዜጠኛ ባቡባከር ቦሪስ ዲዮፕ ያሉ እውቅና ያላቸው ልሂቃን በደብዳቤው ፈራሚነት ከተጠቀሱ 58 አፍሪካውያን ባለሙያዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።
አፍሪካውያኑ ልሂቃን በዚሁ የጋራ ደብዳቤያቸው፤ በፍጥነት እያሽቆለቆለ ነው ያሉት የኢትዮጵያ ሁኔታ “ሐዘን እና ድንጋጤ” እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ያለውን ውጊያ “የእርስ በእርስ ጦርነት” ሲሉ የጠሩት ባለሙያዎቹ፤ ውጊያው በአፍሪካ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንደሚገባ የአፍሪካ ምሁራን ያቀረቧቸውን የተትረፈረፉ ሃሳቦች ግልጋሎት ላይ ላለማዋላቸው ማሳያ ነው ሲሉ ጽፈዋል።
ከደብዳቤው ፈራሚዎች አንዱ የሆኑት በአሜሪካው ቦስተን ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናት ማዕከልን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ሚካኤል ወልደማርያም “ከአስር ገደማ ወራት አድካሚ ግጭት በኋላ በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ቀውስ የበለጠ ይከፋል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። ነገር ግን የትግራይ ጦርነት እየሰፋ እና እየበረታ በሄደበት ጊዜ የተከሰተው ያ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ከደብዳቤው ጋር አብሮ የተሰራጨው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅሷል።
“የግጭቱ ተሳታፊዎች ለህዝባቸው ስቃይ ቅድሚያ ሰጥተው የሚደራደሩበት ጊዜ አሁን ነው” ያሉት ሚካኤል፤ ወደሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እየተስፋፋ የሄደው ቀውስ በኃይል ይፈታል የሚል ሃሳብ “ቅዥት ነው” ሲሉ ተችተዋል። ተመሳሳይ ሀሳብ በተንጸባረቀበት በልሂቃኑ ደብዳቤ ላይም፤ ለቀውሱ መፍትሔው ወታደራዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያው ጦርነት ለመገንባት ረዥም አመታት የወሰዱ ተቋማት እና የባሕል ቅርሶች መውደማቸውን ያወገዙት የአፍሪካ ልሂቃን “የኢትዮጵያ ሕዝቦች በቂ ስቃይ ደርሶባቸዋል። አገሪቱም ከዚህ በላይ ጥፋት ልትሸከም አትችልም” ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል። በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ መባባሱን በደብዳቤያቸው ያነሱት ልሂቃኑ፤ ለጉዳዩ የአፍሪካ ተቋማት እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት የአህጉሩ ተወካይ የሆኑ ሶስት አባል ሀገራት፤ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታቸውን ነቅፈዋል።
አፍሪካውያኑ ልሂቃን፤ ውጊያ የገጠሙት የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ኃይሎችን ጨምሮ በሌሎች ወገኖችም ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ያሏቸውን ሃሳቦችም ደብዳቤያቸው አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት፣ የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግስት እንዲሁም በግጭቱ ተጽዕኖ የደረሰባቸው እና የሚሳተፉ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ቡድኖች ፖለቲካዊ ውይይት እንዲያካሂዱ በተደጋጋሚ ለቀረበላቸው ጥሪ “አዎንታዊ ምላሽ” እንዲሰጡ የደብዳቤው ፈራሚዎች ጠይቀዋል።
በርካታ የአፍሪካ ምሁራን ከግጭት የመውጪያ መንገዶችን መጠቆማቸውን ያስታወሱት ልሂቃኑ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ክልላዊ መንግስት እኒህን ምልከታዎች በበጎ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲያውሏቸው ሃሳብ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ክልላዊ መንግስት፤ በአፍሪካ ህብረት እና በምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አማካኝነት እንዲደራደሩ፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በሁለቱም ወገኖች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደር እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና ኢጋድም ሁለቱን ወገኖች የማሸማገል ኃላፊነታቸውን በንቃት እንዲወጡ ጠይቀዋል። ለዚህም ትላንት ምሽት ይፋ የሆነው የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሚና ሊኖረው እንደሚችል ጠቅሰዋል። የአፍሪካ ህብረት ትላንት ባወጣው መግለጫ፤ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ የህብረቱ ከፍተኛ ልዑክ ሆነው መሾማቸውን ይፋ አድርጓል።
የህብረቱን እና የኢጋድን ጥረት የተቀረው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ መደገፍ እንዳለበት አፍሪካውያኑ ልሂቃን አሳስበዋል። የውጊያው ተሳታፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻዎች ወደ ውይይት ጠረጴዛ እንዲመጡ እና ለፖለቲካዊ መፍትሄ ቁርጠኛ እንዲሆኑ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል። እንዲህ አይነቱ አካሄድ፤ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ወደሚካሄድ መሰረተ-ሰፊ ብሔራዊ ውይይት የሚመራ እንደሚሆንም ልሂቃኑ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)