በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን አምስት ሚሊሺያዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ስር ወዳለችው ቡለን ወረዳ፤ ዛሬ ረፋዱን በባጃጅ ሲጓዙ የነበሩ አምስት ሚሊሺያዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የጉሙዝ ታጣቂዎች አምስት ሚሊሺያዎችን መግደላቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

ሚሊሺያዎቹ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው “ለአካባቢ መጠበቂያ የሚሆን [ትጥቅ] ሊታጠቁ ወደ ከተማው ማዕከል በመጓዝ ላይ እያሉ” መሆኑን አቶ አብዮት ገልጸዋል። በመተከል ዞን ከምትገኘው ዶቤ ቀበሌ እንደተነሱ የተነገረላቸው ሚሊሺያዎች፤ ወደ ቡለን ከተማ ሲጓዙ የነበረው በሶስት ባጃጆች ተሳፍረው ነበር ተብሏል። 

ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የሰነዘሩት በአንደኛው ባጃጅ ውስጥ በነበሩ ሰባት ሚሊሺያዎች ላይ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በጥቃቱም አምስት ሚሊሺያዎች ሲገደሉ፤ ሁለቱ መቁሰላቸውን በቡለን ወረዳ የሚኖሩ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የመንግስት ሰራተኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ጥቃቱ የተፈጸመበት፤ በዶቤ ቀበሌ የሚገኘው በተለምዶ “እሪ በከንቱ” ተብሎ የሚጠራው አካባቢ፤ ከዚህ በፊትም ስጋት ያለበት እና ለትራንስፖርት የማይመች እንደሆነ የሚጠቅሱት ሌላ የቡለን ከተማ ነዋሪ፤ የዛሬው ጥቃት የተፈጸመው “በተጠና መልኩ” ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ለዚህም በማስረጃነት የሚያቀርቡት፤ በቡለን ወረዳ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ትላንት ማምሻውን አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ጥቃቱ መሰንዘሩን ነው። 

በቡለን ወረዳ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ለሌላ ግዳጅ ወደ ጉባ ወረዳ አልመሃል አካባቢ ከተንቀሳቀሰ በኋላ፤ አሁን በስፍራው የሚገኙት የሲዳማ ልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ ብቻ መሆናቸውን ነዋሪው አብራርተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ግን ጥቃቱ ከኃይል እንቅስቃሴው ጋር የተያያዘ “ሊሆንም፤ ላይሆንም ይችላል” ብለዋል።

“ኃይል እንደ አስፈላጊነቱ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሊንቀሳቀስ ይችላል” ያሉት አቶ አብዮት፤ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የልዩ ኃይል አባላት፣ ሚሊሺያዎች እና የታጠቁ ግለሰቦች መኖራቸውን ገልጸዋል። “በአካባቢው የኃይል እጥረት ካለ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ የኃይል እጥረቱ አንዲቀረፍ ማድረግ ይቻላል” ሲሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ አስገንዝበዋል።

“ኃይል እንደ አስፈላጊነቱ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሊንቀሳቀስ ይችላል… በአካባቢው የኃይል እጥረት ካለ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሮ የኃይል እጥረቱ አንዲቀረፍ ማድረግ ይቻላል”

አቶ አብዮት አልቦሮ – የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ

እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን የመከላከያ ሰራዊት ስፍራውን ለቅቆ በመውጣቱ ገና ከአሁኑ ችግሮች መስተዋል መጀመራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በቡለን ከተማ በባጃጅ ሹፌርነት የሚሰራው ሀብታሙ ደሬሳ፤ ከወንበራ እና ሌሎች አካባቢዎች የመጡ በርካታ ሰዎች በስጋት ምክንያት ወደ ሌሎች ቦታዎች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ተናግሯል። 

ሰዎቹ ወደ ቡለን ከተማ የመጡት፤ በመከላከያ ሰራዊት ታጅበው በአማራ ክልል ወደምትገኘው ቻግኒ ከተማ ለመጓዝ እንደነበር የጠቆመው ሀብታሙ፤ ሰራዊቱ አካባቢውን ለቅቆ በመሄዱ መሄጃ ማጣታቸውን አብራርቷል። “እንኳን ያለ አጃቢ [መንቀሳቀስ]፤ ዱር ወጥቶ አንድ ፍየል ይዞ መምጣት አይቻልም” ሲልም በአካባቢው ያለውን የስጋት ደረጃ ገልጿል።

ፎቶ ፋይል፦ የቡለን ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ

የቡለን ወረዳ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ላለው የጸጥታ ስጋት እና ዛሬው ለተፈጸመው ጥቃት ተጠያቂ የሚያደርጉት የጉሙዝ ታጣቂዎችን ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊም “የዛሬውን ጥቃት የፈጸሙት የጉሙዝ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ ወንጅለዋል።

የዛሬውን ጥቃት ያስተናገደችው የቡለን ወረዳ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከሚፈጸምባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች አንዷ ናት። በወረዳዋ ዋና ከተማ ባለፈው ሐምሌ መጀመሪያ በተቀሰቀሰ ግጭት የ14 ሰዎች ህይወት አልፏል። ግጭቱን ተከትሎ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት፤ በቡለን ከተማ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ጭምር ጥሎ ነበር። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት በመተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ ዞኖች በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመግታት፤ ሁሉም የጸጥታ አካላት “የማያዳግም እርምጃ” እንዲወስዱ ከሁለት ሳምንት በፊት ትዕዛዝ ማስተላለፉ አይዘነጋም። በክልሉ የሚገኙ የደቡብ፣ ሲዳማ እና ጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሎች ይሳተፉበታል የተባለው ይህ እርምጃ ኢላማ ያደረገው “ሽብር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ጸረ- ሰላም ኃይሎችን” እንደሆነ የክልሉ መንግስት አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)