በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ መንግስት በሰባት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የቀረጥ እና ታክስ ማሻሻያ አደረገ። ከዛሬ አርብ ነሐሴ 28፤ 2013 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የተገለጸው ማሻሻያው ላልተወሰነ ጊዜ ይቆያል ተብሏል።
ማሻሻያ የተደረገባቸው የምግብ ሸቀጦች ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳር፣ ሩዝ፣ መኮረኒ፣ ፓስታ እና እንቁላል መሆናቸውን የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ዛሬ አርብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። በማሻሻያው መሰረት ስንዴ ከውጭ ሲገባ ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ይሆናል።
የምግብ ዘይት፣ ስኳር እና ሩዝ ከውጭ ሲገቡ እና በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምባቸው፤ ከማንኛውም ቀረጥ እና ታክስ ነጻ እንደሚሆኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቁሟል። ፓስታ እና መኮረኒ ሸቀጦችን በተመለከተ ደግሞ ከውጭ ሲገቡ እና በአገር ውስጥ ግብይት ሲፈጸምባቸው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑ ተገልጿል። የዶሮ እንቁላልም እንዲሁ ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ መሆኑ ተብራርቷል።
መንግስት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያዎችን እና አስተዳደራዊ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ያስታወሱት ዶ/ር እዮብ፤ አሁን የተደረገው ማሻሻያ የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እና ገበያውን ለማረጋጋት አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል። ይህንኑ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግም ለገቢዎች ሚኒስቴር እና ለጉምሩክ ኮሚሽን መመሪያ መተላለፉን ገልጸዋል።
ከታክስ ማሻሻያው በተጨማሪ መንግስት የእነዚህን መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች አቅርቦትን ለመጨመር ሸቀጦቹን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታው በተጨማሪነት አንስተዋል። ለስድስት ወራት ያህል ተፈቅዶ የነበረው፤ ያለውጭ ምንዛሬ ሸቀጦችን የማስገባት አሰራር ለተጨማሪ ስድስት ወራት መራዘሙንም አመልክተዋል።
የታክስ ማሻሻያ ከማድረግ እና አቅርቦትን ከመጨመር ባለፈ መንግስት ገበያውን ለማረጋጋት የገንዘብ ፖሊሲን ጨምሮ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንደሚወስድ ዶ/ር እዮብ በዛሬው መግለጫቸው ይፋ አድርገዋል። ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተላለፈው መመሪያ፤ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ከሚወሰዱ የፖሊሲ እርምጃዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከትናንት በስቲያ ነሐሴ 26፤ 2013 ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ይህ መመሪያ፤ ባንኮች ከሚሰበስቡት የተጣራ ቁጠባ በብሔራዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ የሚገደዱትን የመጠባበቂያ መጠን በፊት ከነበረበት 5 በመቶ በዕጥፍ በማሳደግ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል ያደረገ ነው። በዚህ መመሪያ አማካኝነትም ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበት የወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)