በሃሚድ አወል
በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ማቆያዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ 60 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት እንደሚወስድ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ። ስደተኞቹን በአጠረ ጊዜ ወደ ሀገር ቤት መመለስ ያልተቻለው፤ ለተመላሾች የተዘጋጁት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ባላቸው “ውስን አቅም ምክንያት ነው” ተብሏል።
በሰላም ሚኒስቴር የህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አምባዬ ወልዴ፤ በሳዑዲ አረቢያ ጅዳ በሚገኙ የማቆያ ካምፖች ውስጥ 60 ሺህ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ወደ ስፍራው በተጓዘ አጣሪ ቡድን ጭምር መረጋገጡን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአጣሪ ቡድኑ አባላት ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና ከኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የተውጣጡ ናቸው ብለዋል።

“[ይህ ቁጥር] በእኛ በኩል በተላከው አጣሪ ቡድን የተረጋገጠ ነው። ከዚያም በላይ ዜጎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል” የሚሉት አቶ አምባዬ፤ ቡድኑ የለያቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ስራ በመከናወን ላይ እንዳለ ጠቁመዋል። ነሐሴ 12፤ 2013 በተጀመረው ሁለተኛ ዙር የስደተኞች የመጓጓዝ ሂደት፤ እስካሁን ድረስ አራት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን መመለሳቸውን አስታውቀዋል። ስደተኞችን ወደ አገር ውስጥ በመመለሱ ሂደት ውስጥም ለሴቶች እና ህጸናት ቅድሚያ መሰጠቱን ተናግረዋል።
በሳምንት ሶስት ጊዜ በሚደረጉ በረራዎች፤ በእያንዳንዱ ጊዜ ከ250 እስከ 400 ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ቢሆንም፤ አጠቃላይ ሂደቱ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት እንደሚወስድ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ መመለስ የማይቻለው፤ ለእነርሱ የተዘጋጁት ጊዜያዊ ማቆያ ቦታዎች ያላቸው የማስተናገድ አቅም ውስን በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አቶ አምባዬ አብራርተዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያንን እያስተናገዱ የሚገኙ ጊዜያዊ ማቆያዎች በቁጥር ዘጠኝ ሲሆኑ፤ ሁሉም የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ነው። ወደ እነዚህ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ የሚገቡ ስደተኞች ለአንድ ቀን እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንደሚሸኙ አቶ አምባዬ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት ከሁለት ሺህ በላይ የክልሉ ተወላጅ ስደተኞች በጊዜያዊ ማቆያዎች ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉንም አመልክተዋል። ተመላሾቹ በማቆያዎቹ ውስጥ እንዲሰነብቱ የተደረገው ወደ ክልሉ ለመሄድ የሚያስችል ትራንስፖርት ባለመኖሩ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ። ህወሓት “ወጣቱን እያስገደደ፣ እያፈሰ ወደ ጦርነት እየማገደ ነው” ሲሉ የሚወነጅሉት ኃላፊው፤ ይህ ሁኔታም ከስደት ተመላሾቹ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው እንዳሄዱ ተጨማሪ ምክንያት ነው ይላሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሰላም ሚኒስቴር በሐምሌ ወር በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከሳዑዲ አረቢያ ከተመለሱ ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንድ ሶስተኛ ገደማ የሚሆኑት የትግራይ ክልል ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀው ነበር። ከእነርሱ ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከጊዜያዊ ማቆያ መውጣታቸውን በወቅቱ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)