በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን፤ አምስት የጸጥታ ኃይሎች እና አንድ ቻይናዊ በታጣቂዎች ተገደሉ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አምስት የጸጥታ ኃይሎች በታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ትላንት ረቡዕ ጷጉሜ 3፤ 2013 አመሻሽ ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት፤ በመንገድ ስራ ላይ የተሰማሩ አንድ ቻይናዊ እና ኢትዮጵያዊ መገደላቸውንም ገልጸዋል።  

እንደ አቶ አብዮት ገለጻ፤ በትላንቱ ጥቃቱ የተገደሉት የጸጥታ ኃይሎች፤ አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል እና አራት የፌደራል ፖሊሶች ናቸው። ከእነርሱ በተጨማሪ ሁለት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል። 

የግልገል በለስ – ጉባ መንገድ ወደ ህዳሴው ግድብ የሚወስድ ዋነኛ መንገድ ነው | ፎቶ፦ www.lissainethiopia.wordpress.com

በጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡት ቻይናዊ እና ኢትዮጵያዊ የመንገድ ሰራተኞች፤ ከግልገል በለስ ወደ ጉባ በሚወስደው የ70 ኪሎ ሜትር መንገድ ስራ ላይ የተሰማሩ እንደነበር አቶ አብዮት ተናግረዋል። የግልገል በለስ – ጉባ መንገድ ከአዲስ አበባ በደብረ ማርቆስ፣ አንጅባራ እና ቻግኒ አድርጎ ወደ ህዳሴው ግድብ የሚወስድ ዋነኛ መንገድ ነው። 

በሰኔ 2009 የተጀመረው የዚህ መንገድ ስራ ግንባታው የሚከናወነው “ሬልዌይ ነምበር ስሪ ግሩፕ” በተባለ የቻይና ኩባንያ አማካኝነት ነው። በሰኔ 2012 ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዞለት የነበረው ይህ መንገድ በ887 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ የነበረ ሲሆን፤ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከመስከረም 2013 ጀምሮ ተቋርጦ መቆየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል። የመንገድ ስራ ፕሮጀክቱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም 35 በመቶ ስራው ተጠናቆ ነበር ብለዋል። 

የ2013 ክረምት ወቅት ሲቃረብ፤ ለሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት መንገዱን መጠገን በማስፈለጉ፤ ስራውን አቋርጦ የነበረው የቻይና ኩባንያ ወደ አካባቢው እንዲመለስ መደረጉን እነዚሁ ምንጮች አስረድተዋል። ኩባንያው የመንገድ ጥገና ስራውን በሚያከናውንበት አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ኃይል ተመድቦ መቆየቱንም ጠቁመዋል።

የ2013 ክረምት ወቅት ሲቃረብ፤ ለሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት የግልገል በለስ – ጉባ መንገድ መጠገን በማስፈለጉ ስራውን አቋርጦ የነበረው የቻይና ኩባንያ ወደ አካባቢው እንዲመለስ መደረጉን ምንጮች ተናግረዋል | ፎቶ ፦www.lissainethiopia.wordpress.com

ካለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ስራውን ሲያከናውን የነበረው የቻይናው ኩባንያ፤ ጥገናውን ያጠናቀቀው ከሳምንት በፊት እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፤ የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመው የኩባንያው ሰራተኞች ከአካባቢው በመውጣት ሂደት ላይ ባሉበት ወቅት እንደሆነ ምንጮቹ አብራርተዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ፤ ለጥቃቱ ተጠያቂ ያደረጉት “የህወሓት ፈረስ ሆነው የሚያገለግሉ፤ የጁንታው ተላላኪዎች” ሲሉ የሚወነጅሏቸውን የጉሙዝ ታጣቂዎችን ነው። 

ከጥቃቱ በኋላ የመከላከያ ሰራዊት እና የልዩ ኃይል አባላት “የተጠናከረ እርምጃ” መውሰዳቸውን የቢሮ ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በእርምጃውም በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልጸዋል። እርምጃ ተወስዶባቸዋል የተባሉ ታጣቂዎችን ብዛት በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው፤ ማምሻውን የተደረገ ውጊያ ስለሆነ ትክከለኛ ቁጥሩን መናገር እንደማይችሉ አስረድተው፤ ሆኖም በእርምጃው ታጣቂ ቡድኑ “ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል” ብለዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተደጋጋሚ ጥቃት ከሚደርስባቸው ዞኖች አንዱ የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመበት የመተከል ዞን ነው

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተደጋጋሚ ጥቃት ከሚደርስባቸው ዞኖች አንዱ የትላንቱ ጥቃት የተፈጸመበት የመተከል ዞን ነው። በዞኑ ባለፉት ሁለት ወራት በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ 26 ሰዎች ተገድለዋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት፤ ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ጥቃት ለመፈጸም በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ትእዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል። 

የክልሉ መንግስት ይህን ትዕዛዙን ካስተላለፈ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ሲፈጸም የትላንትናው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ባለፈው ነሐሴ 25፤ 2013 በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሚሊሺያዎች መገደላቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)