በሃሚድ አወል
በአማራ ክልል የሚገኙ አንድ ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች፤ በ2014 የትምህርት ዘመን ትምህርታቸውን መከታተል እንደማይችሉ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ ለመሆን የተገደዱት፤ በአማራ ክልል ባለው ውጊያ “በርካታ” ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ምክንያት እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል።
የትምህርት ቢሮ ኃላፊው፤ ለትምህርት ቤቶቹ ውድመት “ወራሪዎች” ሲሉ የሚጠሯቸውን የትግራይ አማጽያንን ተጠያቂ አድርገዋል። አማጽያኑ “የትምህርት ተቋማትን እየዘረፉ እና እያወደሙ ነው” ሲሉ የሚወነጅሉት ዶ/ር ይልቃል፤ ለዚህም በእነርሱ ቁጥጥር ስር ቆይተው በተለቀቁ የአማራ ክልል አካባቢዎች የደረሰውን ጉዳት በማስረጃነት ጠቅሰዋል።
እስካሁን ባሰባሰቡት መረጃ መሰረት በአማጽያኑ ቁጥጥር ስር በነበሩ አካባቢዎች የሚገኙ 268 ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው መረጋገጡን ዶ/ር ይልቃል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች በከፊል መጎዳታቸውን አክለዋል።
በአማጽያኑ ከፊል ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን እና ትምህርት ለማስጀመር የክልሉ ትምህርት ቢሮ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ዶ/ር ይልቃል ገልጸዋል። ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን ግን ከወጪ ጋር በተያያዘ “ብዙ ፈተና ያጋጥመናል ብለን እናስባለን” ሲሉ ትምህርት ቤቶቹን ወደነበሩበት መመለስ ቀላል እንደማይሆን ጠቁመዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ለመጠገን በዛሬው ዕለት የ100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። ድጋፉ የሚኒስቴር መስሪያ መስሪያ ቤቱ በመደበኛነት ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪነት የተደረገ ነው ተብሏል።
ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች በዚህን መሰሉ ድጋፍ ጥገና ቢደረግላቸውም፤ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርታቸው ለመመለስ ሌሎች ተግዳሮቶች እንቅፋት እንደሚሆኑ ዶ/ር ይልቃል ያስገነዝባሉ። “ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተማሪዎች ወላጆች ሃብት ንብረታቸውን አጥተዋል” የሚሉት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ፤ “ትምህርት ቤቶቹ ቢኖሩ እንኳን ወላጆች ለልጆቻቸው የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት የሚያስችል አቅም የላቸውም” ሲሉ ያስረዳሉ።
ጦርነቱ ያስከትለዋል ተብሎ የሚፈራው የምግብ እጥረት፤ ሌላው በምክንያትነት የተጠቀሰ ተግዳሮት ነው። “የምግብ እጥረት ባለበት ሁኔታ ተማሪዎች ለመማር ይቸገራሉ” ይላሉ ዶ/ር ይልቃል። ጦርነቱ ራሱ በተማሪዎች ላይ የሚያስከትለው የስነ ልቦና ጫና፤ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመለሱ ሊያደርግ ይችላል ሲሉ ተጨማሪ ምክንያት ነው ያሉትን ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል ያለው ውጊያ ያስከተለው ተጽዕኖ፤ ከሶስት ቀናት በፊት ባለፈው ሰኞ መስከረም 3 በክልሉ በተጀመረው የአዲሱ የትምህርት ዘመን ምዝገባ ወቅት መስተዋሉን የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዋግ ኽምራ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በሰሜን ጎንደር በርካታ ወረዳዎች እና ደቡብ ወሎ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በከፊል የተማሪዎች ምዝገባ እንቅስቃሴ አለመኖሩን የሚገልጹት ዶ/ር ይልቃል፤ ይህም በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር የመጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በአማራ ክልል በአጠቃላይ 9,700 ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፤ እስከባለፈው የ2013 የትምህርት ዘመን ድረስ 5.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በአሁኑ ወቅት በትግራይ አማጽያን ቁጥጥር ስር ባሉት የክልሉ አካባቢዎች ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የሚያስተናግዱ፤ 2,900 ገደማ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የቢሮው መረጃ ይጠቁማል።
የትምህርት ቢሮው ኃላፊ “እነዚህም ትምህርት ቤቶች ባናውቀው ነው እንጂ ከጉዳት ነጻ ላይሆኑ ይችላሉ” ሲሉ አማጽያኑ በትምህርት ቤቶቹ ላይ ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላል የሚል ግምት እንዳሉ ይናገራሉ። በአማጽያኑ ስር ያሉት አካባቢዎች ነጻ ሲወጡ፤ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች ብዛት ሊያሻቅብ ይችላል የሚል ስጋት አለ ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)