በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን፤ በቆቦ ከተማ እና በዙሪያው ባሉ የገጠር አካባቢዎች “የቤት ለቤት አሰሳ እና ግድያ መፈጸሙን” የሚገልጹ ሪፖርቶች እንደደረሱት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ሪፖርቶቹ በእነዚህ አካባቢዎች ከግድያ በተጨማሪ ዝርፊያ እና በመሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እንዳመላከቱም ገልጿል።
ኢሰመኮ ይህን ያስታወቀው ዛሬ እሁድ መስከረም 9፤ 2014 ባወጣው አጭር መግለጫ ነው። በቆቦ እና በአካባቢው የተፈጸመው ጥቃት “በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ” እንደሆነ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ድርጊቱ በ“እጅጉ የሚያሳስብ” ነው ብሏል። ኢሰመኮ ጥቃቱን የፈጸሙት “የህወሓት ኃይሎች እንደሆኑ እንደሚነገር” በመግለጫው ቢጠቅስም፤ በራሱ ምርመራ ይህንኑ ስለማረጋገጡ ማብራሪያ አልሰጠም።
በአማራ ክልል የህወሓት ኃይሎች ፈጽመዋቸዋል በሚባሉ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን በተመለከተ ኢሰመኮ መግለጫ ሲያወጣ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ኮሚሽኑ ከአስር ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ በተፈጸመ ጥቃት፤ ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎችን እና ባለስልጣናትን ዋቢ ያደረገው ኮሚሽኑ፤ ጥቃቱን የፈጸሙት የህወሓት ኃይሎችን ናቸው መባሉን በመግለጫው ጠቅሶ ነበር።
ኢሰመኮ በዛሬውም ሆነ በቀደመው መግለጫው፤ በግጭቱ የሚሳተፉ ወገኖች “ሲቪል ሰዎችን የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዲያከብሩ” አሳስቧል። ኮሚሽኑ የዳባቱን ጥቃት የሚመረምር ቡድን ወደ ስፍራው እንደሚልክ አስታውቆ የነበረ ሲሆን፤ በቆቦ እና አካባቢው የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ደግሞ የሚያደርገውን ምርመራ እንደሚቀጥል በዛሬው መግለጫው ጠቁሟል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ እነዚህን ምርመራዎች በገለልተኝነት እንደሚያከናውን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፤ በህወሓት ኃይሎች ግን ተቀባይነት አላገኘም። ኢሰመኮ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በትግራይ ክልል ሲያከናውነው የነበረው ምርመራ መጠናቀቁን ይፋ ካደረገ ከአራት ቀናት በኋላ በትግራይ ክልል መንግስት ስም የተሰራጨ መግለጫም ይህንኑ አስተጋብቷል። በህወሓት የሚመራው የክልሉ መንግስት ባወጣው በዚሁ መግለጫ በምርመራው ላይ ኢሰመኮ መሳተፉን እንደሚቃወም አስታውቆ ነበር። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)