የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጠየቀ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)፤ የክልሉ ገዢ ፓርቲ እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ክልላዊ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረቱ ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው ጥሪውን ያቀረበው፤ በክልሉ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ያገኘ ፓርቲ ባለመኖሩ “የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር” በማሰብ እንደሆነ አስታውቋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ካለው 99 መቀመጫዎች ውስጥ ባለፈው ሰኔ 14፤ 2013 ምርጫ የተካሄደው ለ34 ያህሉ ብቻ ነው። ከእነዚህ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ብልጽግና ፓርቲ ሃያ ስምንቱን ሲያሸነፍ በስድስቱ በድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ተወስኖ ነበር።

በጸጥታ ችግር ምክንያት ሰኔ 14 ምርጫ ባልተደረገባቸው በመተከል እና በካማሺ ዞኖች እንዲሁም በድጋሚ በሚደረግባቸው የአሶሳ ዞን አካባቢዎች በመጪው መስከረም 20 የድምጽ መስጠት ሂደት ይከናወናል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ይህ የቦርዱ ውሳኔ ግን በቀጣይ የሚመሰረተውን የክልሉን መንግስት ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶታል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ካለው 99 መቀመጫዎች ውስጥ ሰኔ 14 ምርጫ የተካሄደው 34 ያህሉ ብቻ ነው | ፎቶ፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት መሰረት፤ የክልሉን መንግስት መመስረት የሚችለው የክልሉን ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ ፓርቲ ነው። ሰኔ 14 በክልሉ በከፊል በተካሄደው ምርጫ ግን ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ያገኘው የመቀመጫ ብዛት ከሃምሳ በመቶ በታች መሆኑ፤ በቀጣይ ክልሉን “በመንግስትነት ማን ይመራዋል?” የሚል ጥያቄ አስነስቷል። 

በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይህንኑ ጉዳይ በማስመልከት ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ገዢው ፓርቲ ከመስከረም 25 በኋላ ክልሉን ማስተዳደር እንደማይችል አስታውቋል። በ2007 የተመረጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የስራ ዘመን ማብቂያው በ2012 እንደነበር ፓርቲው አስታውሷል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በተደረገው የህገ-መንግስት ማሻሻያ፤ የምክር ቤቱ ስልጣን እስከ መስከረም 24፤ 2014 መራዘሙንም ጠቁሟል። 

ለአንድ ዓመት የተራዘመው የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ከሚያበቃበት ከመስከረም 25 በኋላ፤ የክልሉ ገዢ ፓርቲ “በስልጣን ላይ መቆየት አይችልም” ሲል ቦዴፓ በዛሬው መግለጫው አትቷል። በድጋሚ በክልሉ ህገ-መንግስት ላይ ማሻሻያ ማድረግም ሆነ የስልጣን ጊዜ ማራዘም እንደማይቻል የሚከራከረው ፓርቲው፤ ለችግሩ መፍትሄ ናቸው ያላቸውን ሶስት አማራጮች ዘርዝሯል።

በ2007 የተመረጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የስራ ዘመን ማብቂያው በ2012 የነበረ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት መራዘሙ ይታወሳል | ፎቶ፦ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል “የአመራር ክፍተት እንዳይፈጠር” በመፍትሄነት ከቀረቡ አማራጮች መካከል በመጀመሪያው ረድፍ የተቀመጠው ክልላዊ የሽግግር መንግስት መመስረት ነው። በዚህ የቦዴፓ አማራጭ መሰረት፤ በክልሉ ምርጫ ተካሄዶ አዲስ ክልላዊ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ የክልሉ ገዢ ፓርቲ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ ክልላዊ የሽግግር መንግስት ይመሰርታሉ።

ሁለተኛው የቦዴፓ አማራጭ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም ነው። ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋም ከሆነ ይህን ኃላፊነት ሊወጡ የሚችሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የፌደሬሽን ምክር ቤት እንደሚሆኑ ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስትም ሆነ የፌደራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበት ስርዓትን ለመደንገግ በ1995 የወጣው አዋጅ ይህንን ለመተግበር የሚያስችሉ እንደሆኑ ፓርቲው አብራርቷል።

ቦዴፓ በመጨረሻ ያቀረበው አማራጭ፤ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ገለልተኛ የሆነ ጊዜያዊ ባለ አደራ መንግስት ማደራጀትን ነው። የባለ አደራ መንግስቱ በክልሉ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ በስልጣን ላይ የሚቆይ ይሆናል ብሏል ፓርቲው። 

“ካቀረብናቸው ህገ መንግስታዊ አማራጮች ሌላ አማራጭ አለ ብለን አናምንም” ያለው ተቃዋሚ ፓርቲው፤ በጉዳዩ ላይ “በፍጥነት ውይይት እና ድርድር” እንዲጀመር ጠይቋል። “በህዝብ ሳይመረጥ ከመስከረም 25 በኋላ ክልሉን ለመምራት የሚደረግ ማንኛውም ህገወጥ አካሄድ ተቀባይነት የለውም” ሲልም አቋሙን በግልጽ አስታውቋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ዐቃቤ ህግ በትላንትው ዕለት በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በክልሉ በመስከረም 20 ምርጫ ባለመካሄዱ “ ‘መንግስታዊ መዋቅር አይኖርም’ በሚል፤ ሁከት ለመፍጠር እና ግጭት ለማስነሳት” የተዘጋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ ሲሉ ወንጅለዋል። ከቦዴፓ መግለጫ አንድ ቀን ቀድሞ የተሰራጨው ይህ መግለጫ፤ ፓርቲዎቹ ከዚህን መሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል። ፓርቲዎቹ በክልሉ ለሚፈጠሩ “የጸጥታ ችግሮች ኃላፊነት ይወስዳሉ” ሲልም አስጠንቅቋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተደጋጋሚ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው እና ግጭቶች ከሚፈጠሩባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ዋነኛው ነው። በክልሉ በ2013 የመጨረሻ ሁለት ወራት ብቻ ከ30 በላይ ሰዎች በታጣቂዎች ተገድለዋል። እንዲሁም በ2013 መጨረሻ በአስር ቀናት ልዩነት በተፈጸሙ ሁለት ጥቃቶች ምክንያት አስር የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)