በወላይታ ሶዶ ከተማ አቅራቢያ የአውሮፕላን ማረፊያ ሊገነባ ነው

በሃሚድ አወል

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አቅራቢያ ላይ በሚገኝ ቦታ ላይ አዲስ የአውሮፕላን ማረፊያ ሊገነባ ነው። የወላይታ ዞን አስተዳደር ለአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ የሚውለውን 150 ሄክታር ቦታ ትላንት ሐሙስ መስከረም 13 ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስረክቧል።

የአየር ማረፊያው የሚገነባው ከወላይታ ሶዶ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ላሾ በተባለ አካባቢ እንደሆነ የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል። አካባቢው የሶዶ ዙሪያ እና የዳሞት ሶሬ ወረዳዎችን የሚያዋስን ነው።

የአየር ማረፊያው የሚገነባበት ቦታ በወላይታ ዞን ስር ያሉትን የሶዶ ዙሪያ እና የዳሞት ሶሬ ወረዳዎችን የሚያዋስን ነው | ፎቶዎች፦ የወላይታ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

ቤድሮክ በተባለ አገር በቀል ኮንስትራክሽን ድርጅት የሚከናወነው የአየር ማረፊያ ግንባታ በሶስት ምዕራፎች የተከፋፈለ እንደሆነ የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ ዘካሪያስ ታደሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ አማካሪው ገልጸዋል።  

ይህ ወጪ በግንባታው ምክንያት ከቦታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች የሚከፈለውን ካሳ የሚጨምር እንደሆነ አቶ ዘካሪያስ አስረድተዋል። የአውሮፕላን ማረፊያው በሚገነባበት አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች “በጣም ጥቂት ናቸው” የሚሉት አማካሪው፤ ለእነርሱ የሚከፈለው ካሳ የሚወሰነው የዞኑ አስተዳደር የሚያቋቁመው የቴክኒካል ቡድን በሚያደርገው ጥናት መሰረት እንደሆነ አብራርተዋል። 

የወላይታ ዞን አስተዳደር በሶዶ አቅራቢያ ለሚገነባው አየር ማረፊያ የተመደበውን ቦታ ለሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን እና ግንባታውን ለሚያከናውነው ቤድሮክ ኮንስትራክሽን ድርጅት በትላንትናው ዕለት አስረክቧል

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከ1950ዎቹ እስከ 1970ዎቹ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ የአውሮፕላን ማረፊያ ነበራት። ከ20 ዓመታት በላይ መንገደኞችን ሲያስተናግድ የቆየው የአውሮፕላን ማረፊያ አገልግሎቱን ያቋረጠው “ደረጃውን የጠበቀ” ባለመሆኑ ምክንያት እንደነበር የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባልደረባ የሆኑት አቶ ግርማ ጌቾ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።  

የዞኑ ነዋሪዎች ከ1990ዎቹ ጀምሮ የአውሮፕላን ማረፊያ በአካባቢው እንዲገነባ ጥያቄ ሲያቀርቡ ቢቆዩም፤ በ1999 የቀደሞው አውሮፕላን ማረፊያ በነበረበት ቦታ ላይ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ በመገንባቱ የማህበረሰቡ ጥያቄ ሳይመለስ እንዲቆይ አድርጎታል ሲሉ አቶ ግርማ ያብራራሉ። የትላንትናው የቦታ ርክክብ የፊርማ ስነ ስርዓት ለዓመታት የቆየውን የህብረተሰቡ ጥያቄ ይመልሳል ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)