በተስፋለም ወልደየስ
የምስራቅ ሐረርጌ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ሰዓዳ አብዱራህማን የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያን በአፈ ጉባኤነት እንዲመሩ ተመረጡ። ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 15፤ 2014 የምስረታ ጉባኤውን ያካሄደው ጨፌ ኦሮሚያ፤ አቶ ኤልያስ ኡመታን ምክር ቤቱን በምክትል አፈ ጉባኤነት እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል።
የአፈ ጉባኤዋን ምርጫ 453 የጨፌ አባላት የደገፉት ሲሆን ከአንድ አባል ተቃውሞ ገጥሞታል። ሌላ አንድ የምክር ቤት አባልም ድምጸ ተዐቅቦ አድርገዋል። በምክትል አፈ ጉባኤነት የተመረጡት አቶ ኤልያስ ከሰባት የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ የገጠማቸው ሲሆን ዘጠኝ አባላት ደግሞ ለእርሳቸው ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።
የሁለቱን ተመራጮች የቀደመ የስራ ኃላፊነት እና የትምህርት ዝግጅታቸውን ለምክር ቤቱ በዝርዝር ያቀረቡት፤ የኦሮሚያ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ በሆኑት አቶ ፍቃዱ ተሰማ ነበሩ። የፓርቲው ቃል አቃባይ አቶ ታዬ ደንደአ፤ አፈ ጉባኤዎቹ በተመረጡበት አካሄድ እና ብቃታቸው ላይ ያልተጠበቀ ተቃውሞ አሰምተዋል።
አፈ ጉባኤዎቹ ለቦታው ሲታጩ በፓርቲው ውስጥ ያሉ እንደ እርሳቸው አይነት ሰዎች የሚያውቁት ነገር እንዳልነበር ለምክር ቤቱ የተናገሩት አቶ ታዬ፤ “በርቀት ያሉ ሰዎች እንዴት እነዚህን ሰዎች ሊመርጡ ቻሉ?” ሲሉ ጠይቀዋል። ሁለቱም ግለሰቦች ከዚህ ቀደም ብዙ ዋጋ መክፈላቸውን እና አሁን ባሉበት የኃላፊነት ቦታ ስራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆኑን እንደሚያውቁ ለምክር ቤቱ ያስረዱት አቶ ታዬ፤ ሆኖም ግለሰቦቹ ለቦታው ይመጥናሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል።
“ጨፌ ኦሮሚያን መምራት ማለት ኢትዮጵያን እንደ ማንቀሳቀስ ማለት ነው” ሲሉ አጽንኦት የሰጡት አቶ ታዬ፤ ለአፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤነት የቀረቡት ግለሰቦች “ለቦታው ብቃት ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም” ሲሉ ምርጫውን ተቃውመዋል።
ተቃውሞውን ተከትለው አስተያየት የሰጡት አቶ ሁሴን ፈይሶ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ ሁለቱም ዕጩዎች ለቦታው ተግኒ መሆናቸውን በመጥቀስ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል። ለአቶ ታዬ ተቃውሞ ምላሽ የሰጡት የኦሮሚያ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ የሁለቱ ዕጩዎች አመራረጥ የፓርቲ አሰራርን በተከተለ መልኩ በአግባቡ የተካሄደ ነው ብለዋል። “ዋናው አመለካከታቸው ነው” ሲሉም ዕጩዎቹ የተመረጡበት ዋነኛ መስፈርት የፖለቲካ አቋማቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።
የዛሬዎቹ ተመራጮች የተኳቸው አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ እና ምክትላቸውን መሃቡባ አደምን ነው። ወ/ሮ ሎሚ ጨፌ ኦሮሚያን በአፈ ጉባኤነት ያገለገሉት ላለፉት ሶስት ዓመታት ነው። ተሰናባቿ አፈ ጉባኤ የክልሉን ምክር ቤት የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት በመስከረም 2011 በተደረገ አስቸኳይ ስብሰባ ነበር። በወቅቱ አፈ ጉባኤ የነበሩት አቶ እሸቱ ደሴ “ተደራራቢ የስራ ኃላፊነት አለባቸው” በሚል ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል።
የጨፌ ኦሮሚያን ከዚህ ቀደም በአፈ ጉባኤነት ከመሩ ግለሰቦች ውስጥ አቶ ለማ መገርሳ እና ደሚቱ ሀምቢሳ ይጠቀሳሉ። አቶ ለማ ከዚህ ኃላፊነታቸው በኋላ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት እና የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። ከአፈ ጉባኤ ኃላፊነታቸው በኋላ ከክልል ወደ ፌደራል የመጡት ወ/ሮ ደሚቱም፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል። በጣሊያን አምባሳደር ሆነው ከመሾማቸው በፊትም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቤኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)