በሃሚድ አወል
የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴርን ላለፈው አንድ አመት ከመንፈቅ በሚኒስትርነት የመሩት ፊልሰን አብዱላሂ ስልጣናቸውን በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አስታወቁ። ሚኒስትሯ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ የወሰኑት ከህሊናቸው ውሳኔ ጋር በተያያዘ የግል ምክንያት መሆኑን ቢገልጹም፤ ለፌደራል መንግስት ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ግን አዲስ በሚመሰረተው መንግስት መስሪያ ቤታቸው በመታጠፉ ምክንያት የተነሳ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል።
ሚኒስትር ፊልሰን ከስራቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት፤ በይፋዊ የፌስቡክ እና ትዊተር ገጾቻቸው ባጋሩትን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ነው። ዛሬ ሰኞ መስከረም 17፤ 2014 መጻፉ በተገለጸው የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ ላይ በተቀባይነት የተጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው።
ባለ አንድ ገጹ የስራ መልቀቂያ ደብዳቤ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር አርማን የያዘ ሲሆን የሚኒስትሯን ፊርማ እና ማህተም አካትቷል። በደብዳቤው በቅድሚያ የተነሳው ጉዳይ፤ ሚኒስትሯ በሚመሩት መስሪያ ቤት ያጋጠማቸውን ተግዳሮት እና ያስመዘገቡት ወጤት ነው።
“ውስን የሰው ኃይል እና በቂ በጀት ያልነበረውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለመምራት እና ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ኃላፊነትን መቀበል፤ ራስን ለውድቀት እንደማዘጋጀት ስሜት አለው” ሲሉ ፊልሰን በደብዳቤያቸው ጽፈዋል። መሰናክሎች እና ችግሮች ቢኖሩም፤ በአንድ አመት ውስጥ ብዙ እርምጃ መጓዛቸውን በኩራት ገልጸዋል።
ሚኒስትሯ ለዚህ በማሳያነት የጠቀሱት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላትና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ማደሱ እና የ10 ዓመት መሪ እቅድ ማዘጋጀቱን ነው። መስሪያ ቤቱ ያዘጋጃቸው እቅዶች እና ተነሳሽነቶችን መተግበር የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶችን መብቶች እና ደህንነት ለማስከበር እንደሚያስችል ጠቁመዋል። ይህ ጉዳይ ከምንጊዜውም በበለጠ፣ በዚህ አንገብጋቢ ጊዜ በሀገሪቱ ውስጥ ወሳኝ እንደሆነም አብራርተዋል።
ሚኒስትሯ የስራ መልቀቅ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በበርካታ ሀገራዊ እና ተቋማዊ ጉዳዩች ላይ ያደረጓቸውን ውይይቶች ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባታቸውን በደብዳቤያቸው ላይ ጠቅሰዋል። በማንኛውም የስራ ጫና እና ውጥረት ውስጥ ከመስራት ባለፈ፤ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አብሮ በመስራት እና ኃላፊነት መልቀቅ አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ጠቃሚ እንደሚሆን አትተዋል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ይስማማሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
“መርሆዬን ለድርድር የሚያቀርብ ማንኛውም ሁኔታ፤ ከእኔ እምነት እና እሴት ጋር ይቃረናል” ያሉት ወጣቷ ሚኒስትር፤ “እነዚህን እምነቶች አሳልፎ መስጠት የራሴን እና የዜጎቻችን አደራ መጣስ ነው” ሲሉ ከስራ መልቀቃቸው ጀርባ ያለውን ምክንያት በደፈናው ገልጸዋል። ሚኒስትሯ የትኛውን መርሆ አሊያም እምነት ለመጣስ እንደተገደዱ ግን በደብዳቤያቸው ላይ ሳይገልጹ አልፈዋል።
ሚኒስትር ፊልሰን የስራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ማስገባታቸውን ያስታወቁት፤ አዲሱ የፌደራል መንግስት ሊመሰረት የአንድ ሳምንት ብቻ በቀረበት በዚህ ጊዜ ነው። በመጪው ሳምንት ሰኞ መስከረም 24 የሚደረገው አዲሱ የፌደራል መንግስትን ምስረታን ተከትሎ፤ በተወሰኑ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አወቃቀር ላይ ማሻሻያ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አዲሱ ማሻሻያ ከሚነካቸው መስሪያ ቤቶች መካከል የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስቴር እንደዚሁም የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚገኙበት እነዚሁ ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል። የሚኒስትር ፊልሰን የስራ መልቀቅ ውሳኔም “መስሪያ ቤታቸው ታጥፎ በሌላ አወቃቀር ውስጥ ከመግባቱ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ይህንን መረጃ በተመለከተ የሚኒስትሯን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።
የሶማሌ ክልል ተወላጅ የሆኑት ፊልሰን አብዱላሂ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት መጋቢት 3፤ 2012 ነበር። ፊልሰን የሚኒስትርነት ወንበሩን የተረከቡት በወቅቱ በፌደራል መንግስት ካቤኔ ውስጥ ብቸኛ የህወሓት አባል የነበሩትን የአለም ጸጋዬን በመተካት ነበር።
በፌደራል መንግስት ካቢኔ ውስጥ በወጣትነት በመሾም መነጋገሪያ ሆነው የነበሩት ፊልሰን፤ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት እውቅና ያገኙት “ነበድ” የተባለውን የቴሌቪዥን ጣቢያ በማቋቋም ነበር። በሶማሌኛ ቋንቋ የሚተላለፈው ይህ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ በማህበረሰቦች መካከል ሰላምን ለመፍጠር በማለም የተመሰረተ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ተስፋለም ወልደየስ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]