አዳነች አቤቤ የመጀመሪያዋ ሴት የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው ተመረጡ

በሃሚድ አወል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አዳነች አቤቤን የአዲስ አበባ ከንቲባ አድርጎ መረጠ። አዲስ አበባ በከንቲባ መተዳደር ከጀመረችበት ከ1901 ጀምሮ ሴት ከንቲባ ስታገኝ ይህ የመጀመሪያዋ ነው። 

ከንቲባይቱ የተመረጡት ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 18፤ 2014 በተከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤ ላይ ነው። የአዲስ አበባ ምክር ቤት አዳነች አቤቤን ከንቲባ አድርጎ የመረጠው በሙሉ ድምጽ ነው።

አዳነች የአዲስ አበባን የከንቲባነት ስልጣን ከመረከባቸው አስቀድሞ፤ ላለፈው አንድ ዓመት ከተማይቱን በምክትል ከንቲባነት ሲመሩ ቆይተዋል። መዲናይቱ አዲሷቷን መሪ በከንቲባነት ከመቀበሏ በፊት የ30 ከንቲባዎችን የስልጣን ዘመን አስተናግዳለች። 

አዲስ አበባን ከመቶ አመታት በላይ ሲያስተዳድሩ ከነበሩት ከንቲባዎች መካከል ስድስቱ የደጃዝማችነት ማዕረግ የነበራቸው ሲሆኑ ሶስቱ ቢተወደዶች ነበሩ። ከተማይቱ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት የራስ ማዕረግ ባላቸው ሶስት ከንቲባዎች መመሯቷን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ሰባት ከንቲባዎች የተፈራረቁባት አዲስ አበባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ስትመራ የቆየችው በምክትል ከንቲባዎች ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያዎቹ አራት የስልጣን ወራት በአዲስ አበባ ከንቲባነታቸው የጸኑት አቶ ድሪባ ኩማ፤ የስልጣን ዘመናቸውን በማጠናቀቃቸው ለከተማይቱ አዲስ አስተዳዳሪ መፈለግ ግድ እንዲል አድርጎታል። 

በወቅቱ በገዢው ፓርቲ አዲስ አበባን እንዲመሩ የታጩት አቶ ታከለ ኡማ ነበሩ። ወጣቱ የገዢው ፓርቲ ዕጩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል አለመሆናቸው፤ በከንቲባነት እንዳይሾሙ እንቅፋት ቢሆንባቸውም አዲስ አበባን ከመምራት ግን አላገዳቸውም። የፌደራል ፓርላማ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር ላይ ባደረገው ማሻሻያ አማካኝነት፤ አቶ ታከለ በምክትል ከንቲባነት አዲስ አበባን ለሁለት ዓመታት እንዲያስተዳድሩ ተደርጓል።

አቶ ታከለን ተክተው ወደ ከተማዋ አስተዳዳሪነት ስልጣን የመጡት ወይዘሮ አዳነችም፤ በተመሳሳይ አካሄድ ከተማይቱን ለአንድ ዓመት መርተዋል። አዳነች የመሪነት ቦታውን የተረከቡት በነሐሴ 2012 በተደረገ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ነው። የምክር ቤቱ ተመራጭ ያልነበሩት አዳነች፤ ከተማይቱን በምክትል ከንቲባነት እንዲመሩ የውሳኔ ሀሳብ ሲቀርብ ስድስት የምክር ቤት አባላት በወቅቱ ተቃውመው ነበር።

ምክትል ከንቲባዋ ከአንድ ዓመት የመሪነት ጊዜ በኋላ በተደረገው አጠቃላይ ምርጫ፤ የአዲስ አበባ ምክር ቤት መቀመጫን ለማግኘት ተወዳድረዋል። ሰኔ 14፤ 2013 በተካሄደው ምርጫ አሸናፊ ሆነውም የአዲስ አበባን ምክር ቤት ተቀላቅለዋል። አዳነች በተወዳደሩበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ የምርጫ ክልል ድምጽ ከሰጡ ከ200 መቶ ሺህ  በላይ መራጮች መካከል፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለምክትል ከንቲባዋ ድምጽ መስጠታቸውን የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።

አዳነች አቤቤ ወደ አዲስ አበባ አስተዳደር ከመዛወራቸው በፊት፤ በፌደራል ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቤኒ አባል ነበሩ። ለስድስት ወራት ካገለገሉበት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግነት የኃላፊነት ቦታ አስቀድሞ፤ በገቢዎች ሚኒስትርነት ለአንድ ዓመት ሰርተዋል።  

አዲሷ የአዲስ አበባ ከንቲባ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል። አዳነች በኦሮሚያ ክልል በዐቃቤ ህግነት የሰሩ ሲሆን በክልሉ ፍትህ ቢሮም እስከ ምክትል ኃላፊነት ደረጃ ደርሰዋል። በኦሮሚያ ክልል የሰራተኛና ማህበራዊ ቢሮ ኃላፊም ነበሩ። አዳነች በአዳማ ከተማ ከንቲባነት በነበራቸው ቆይታ ዝናን እንዳተረፉ ይነገርላቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)