የአዲስ አበባ ምክር ቤት አዲስ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ መረጠ

የአዲስ አበባ ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው የምስረታ ጉባኤ፤ አዲስ አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈጉባኤ መረጠ። የፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ቡዜና አልቃድር የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ሆነው ሲመረጡ፤ አዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወይዘሮ ፈይዛ መሐመድ ደግሞ ምክትላቸው ሆነዋል። 

ምክር ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 18 በካሄደው ጉባኤ፤ ሁለቱንም አፈ ጉባኤዎች የመረጠው በሙሉ ድምጽ ነው። ወይዘሮ ቡዜና ላለፉት አስራ አንድ ወራት ምክር ቤቱን በአፈ ጉባኤነት ያገለገሉትን ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ በመተካት ምክር ቤቱን የመምራት ስልጣን ተረክበዋል።  

የ47 ዓመቷ አፈ ጉባኤ ከዚህ ቀደም የአሶሳ ከተማ የምክር ቤት አባል ነበሩ። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ኃላፊነትም ሰርተዋል። አዲሷ አፈ ጉባኤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት ያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በሊደርሺፕ እና ጉድ ገቨርናንስ ተቀብለዋል።

የእርሳቸው ምክትል በመሆን የተመረጡት ፈኢዛ፤ በኢኮኖሚክስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል። ምክትል አፈ ጉባኤዋ በቢዝነስ አስተዳደርም ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)