በሃሚድ አወል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች የተካተቱበትን ካቢኔ አቋቋመ። ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮቹ በተጨማሪ፤ ሁለት የፌደራል ሚኒስትሮችም የአዲሱ ካቢኔ አካል ሆነዋል።
በከንቲባ አዳነች አቤቤ አቅራቢነት፤ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 18፤ 2014 ሹመታቸው የጸደቀላቸው ተሿሚዎች ብዛት 26 ነው። ከሃያ ስድስቱ የካቢኔ አባላት መካከል ስምንቱ ሴቶች ናቸው። የካቢኔ አባላቱ ሹመት የአብዛኞቹን የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ አግኝቷል።
በአዲሱ የአዲስ አበባ ካቢኔ ምስረታ፤ የኢዜማ እና የአብን አመራሮች መሾማቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ሰኔ 14፤ 2013 በተደረገው ምርጫ፤ ገዢው ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ያሉትን 138 መቀመጫዎች በሙሉ ጠራርጎ በማሸነፉ ተቃዋሚዎች ወደ ኃላፊነት የመምጣት ዕድላቸውን ያጨለመ መስሎ ነበር።
አዲሷ የአዲስ አበባ ከንቲባ፤ በካቢኔያቸው ያካተቷቸውን ተሿሚዎች ዝርዝር ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት ግን ይህን አመለካከት የሚያፈርስ አካሄድ መከተላቸው ታይቷል። ገዢው ፓርቲ የህዝብን ድምጽ ለማክበር ተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደሚያሳትፍ ቃል መግባቱን ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ ይህንን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምስረታ ላይ ተግባራዊ ማድረጉን አስረድተዋል።
በዚህ ውሳኔ መሰረት በአዲስ አበባ ካቢኔ ውስጥ ሹመት ያገኙት የኢዜማ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ እና የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ናቸው። አቶ ግርማ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን እንዲመሩ ሲሾሙ፤ አቶ የሱፍ ደግሞ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ኃላፊ ሆነዋል።
ሁለቱም ተሿሚዎች፤ የከተማይቱ የካቢኔ አባላት ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት በአካል አለመቅረባቸው አጠያይቋል። አቶ ግርማ ሰይፉ በሹመት ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳልተገኙ የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
ሹመቱን በተመለከተ ፓርቲያቸው ያስተላለፈው ውሳኔ ምን እንደነበር የተጠየቁት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ በኢዜማ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ውሳኔ የሚሰጠው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መሆኑን ገልፀዋል። የኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ በመጪው ቅዳሜ እና እሁድ የሚካሄድ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ናትናኤል፤ በዚህም ምክንያት የአቶ ግርማ ሹመት በፓርቲው ገና አልጸደቀም ብለዋል።
ኢዜማ “ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመስራት መርህ አለው” የሚሉት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ የአቶ ግርማ ሹመት በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ሳይጸድቅ፤ በአዲስ አበባ ካቢኔ ምስረታ ላይ መነገሩ “በመርህ ደረጃ የሚያመጣው ችግር የለም” ብለዋል። አካሄዱን ግን “በአፈፃፀም ደረጃ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት” ሲሉ ጠርተውታል። በጉዳዩ ላይ በኢዜማና በገዢው ብልፅግና መካከል የመረጃ ክፍተት እንደነበርም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
ዛሬ የተመሰረተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በተጨማሪ በሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩ ሁለት የፌደራል መንግስት ባለስልጣናትን ማካተቱ ሌላው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኗል። የአዳነች አቤቤን ካቢኔ የተቀላቀሉት ሁለት ሚኒስትሮች የመከላከያ እንዲሁም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ሲመሩ የነበሩ ባለስልጣናት ናቸው።
አቶ ለማ መገርሳን ተክተው የመከላከያ ሚኒስቴር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ቀነዓ ያደታ፤ የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሂሩት ካሳው ደግሞ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮን የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
በዛሬው የካቢኔ ምስረታ ከታዩ ነገሮች አንዱ ቀደም ሲል ተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ይዘው የነበሩ ባለስልጣናት በነበሩበት እንዲቀጥሉ የመደረጉ እውነታ ነው። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ሆነው ላለፈው አንድ ዓመት ሲሰሩ የቆዩት አቶ ጃንጥራር አባይ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነዋል።
አቶ ጃንጥራር በዛሬው ሹመት ከምክትል ከንቲባነት በተጨማሪ የአዲስ አበባ የስራ ኢንተርፕራይዝ እና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊነትን ደርበው እንዲሰሩ ተሹመዋል። የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ጥራቱ በየነ፤ በነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ስልጣናቸው ቀጥለዋል። የጤና ቢሮ ኃላፊው ዶ/ር ዮሃንስ ጫላ፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዘላለም ሙላቱ እና የገቢዎች ቢሮ ኃላፊው አቶ ሙሉጌታ ተፈራም እንዲሁ በያዙት ቦታ እንዲቀጥሉ ተወስኗል።
ዛሬ አዲስ በተመሰረተው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አወቃቀር መሰረት፤ አቶ ጥራቱን ጨምሮ አራት የስራ ኃላፊዎች የምክትል ከንቲባ ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል። በገንዘብ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታነት ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሆነዋል።
ሌላኛዋ የምክትል ከንቲባ ማዕረግን የያዙት ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን ደግሞ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በኃላፊነት እንዲመሩ ተሹመዋል። በአዲስ አበባ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊነት ስልጣን ያገኙት ወይዘሮ ነጂባ አክመልም የምክትል ከንቲባ ማዕረግን በማግኘት ሶስተኛዋ ሴት ሆነዋል።
ምክር ቤቱ የካቢኔ አባላትን ሹመት ከመመልከቱ አስቀድሞ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት እና ስልጣንና ተግባራቸውን ለመዘርዝር የወጣውን አዋጅ አጽድቋል። በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው እና በሰባት ክፍሎች እና 100 አንቀጾች የተዋቀረው አዲሱ አዋጅ፤ በከተማዋ ያሉትን የአስፈጻሚ አካላት ቁጥር ከ61 ወደ 46 ዝቅ አድርጓቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)