በሃሚድ አወል
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሲዳማ ክልል ለፓርላማ የተወዳደሩ ሁለት ተመራጮች፤ በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ወደሚከፈተው የተወካዮች ምክር ቤት ላይገቡ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) አመራሮች የሆኑት ሁለቱ ግለሰቦች፤ በፓርቲያቸው እና በሲዳማ ብልጽግና መካከል ያለው የቅንጅት ሂደት እልባት ካላገኘ ወደ ፓርላማ ላለመግባት መወሰናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከመቀላቀላቸው በፊት ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ እንዲሟላ የጠየቁት የፓርላማ ተመራጮች፤ አቶ ሰላሙ ቡላዶ እና አቶ ደሳለኝ ሜሳ ናቸው። የሲአን ኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰላሙ በሲዳማ ክልል በቡርሳ ምርጫ ክልል ተወዳድረው ያሸንፉ ሲሆን፤ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ደግሞ በቱላ ምርጫ ክልል ለፓርላማ የተመረጡ ናቸው።
ሁለቱ ተመራጮች ባለፈው ሰኔ ወር በተካሄደው ምርጫ ለውድድር የቀረቡት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው እንደነበር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያሳያል። የሲዳማ ክልል በተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን 19 መቀመጫዎች ሙሉ ለሙሉ ያሸነፈውም ገዢው ፓርቲ ነው።
ሁለቱ የሲአን ከፍተኛ አመራሮች በብልጽግና ስም ለምርጫ የቀረቡት፤ ፓርቲያቸው ከሲዳማ ብልጽግና ፓርቲ ጋር የፈጠረው ቅንጅት “በፍጥነት ዕውቅና ያገኛል” ብለው በማሰባቸው እንደነበር ያስረዳሉ። የፓርቲያቸው አመራሮች “የዕጩ ማስመዝገቢያ ጊዜ እንዳያልፍ” በሚል እንደ ብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች እንዲመዘገቡ እንደነገሯቸው አቶ ደሳለኝ ይናገራሉ። “የቅንጅቱ ጉዳይ ከዚያ በኋላ ያልቃል” የሚል ቃል እንደተገባላቸውም መልስ ብለው ያስታውሳሉ።
የሲአን እና ብልጽግና ቅንጅት ጉዳይ መነሳት የጀመረው ከሲዳማ ክልል ምስረታ ማግስት ጀምሮ ነው። ሲአን ለገዢው ፓርቲ ያቀረበው “የአብረን እንስራ” ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በመቆየቱ፤ ተቃዋሚ ፓርቲው ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ የራሱን ዕጩዎችን ምልመላ ጨርሶ እንደነበር ሁለቱ የፓርላማ ተመራጮች ይገልጻሉ። የምርጫ ዕጩዎች ምልመላው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን በሲዳማ ብልጽግና ሀሳብ አመንጪነት ሁለቱ ፓርቲዎች ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ለመቀናጀት ከውሳኔ ላይ እንደደረሱም ያብራራሉ።
የሲዳማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ማርሻሎ፤ ፓርቲያቸው እና ሲአን ዕጩዎችን በጋራ ለማቅረብ መስማማታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “ዕጩዎቹ [ለውድድር] የቀረቡት በብልጽግና ስም እና ምልክት ነው” ሲሉም የምርጫ ሂደቱን አስረድተዋል።
ሲአን ከሲዳማ ብልጽግና ጋር በመቀናጀት ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዕጩዎችን ማቅረቡን የፓርቲው ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ ለገሰ ላንቃሞም ይቀበላሉ። ነገር ግን የሁለቱ ፓርቲዎች የቅንጅት ጥያቄ ለምርጫ ቦርዱ መቅረብ በነበረበት ጊዜ ባለመቅረቡ፤ ቅንጅቱ በቦርዱ እውቅና አለማግኘቱን ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ፤ ለመቀናጀት የፈለጉ ፓርቲዎች ጥያቄያቸውን ለምርጫ ቦርድ ማቅረብ ያለባቸው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ ሁለት ወራት በፊት መሆኑን ይደነግጋል። የሁለቱ ፓርቲዎች የቅንጅት ጥያቄ ለቦርዱ የቀረበው ግን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ከሆነ ከሶስት ወራት በኋላ እንደሆነ ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የፓርቲዎቹ ቅንጅት በምርጫ ቦርድ ባልጸደቀበት ሁኔታ “የሲአን አባላት ማንን ወክለው ነው ለምርጫ የቀረቡት?” በሚል ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠየቁት የሲአን ጸሀፊ አቶ ለገሰ፤ “ያንጊዜ ነው መጠየቅ የነበረባችሁ፣ አሁን ጊዜው አልፏል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ሁለቱ አባላት የትኛውን ፓርቲ ወክለው ፓርላማ እንደሚገቡ ለተጠየቁትም፤ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ካልሆነ እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው መሰል ጥያቄዎችን እንደማያስተናግዱ ጠቅሰው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሁለቱ የፓርቲው አባላት ግን ከቅንጅቱ ጋር በተያያዘ ያስቀመጧቸው ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ፤ በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ የሚመሰረተው የፌደራል መንግስት ፓርላማ አካል እንደማይሆኑ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የቡርሳ ምርጫ ክልል ተመራጩ አቶ ሰላሙ “ሁለቱ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በፍጹም አንገባም” ሲሉ አቋማቸውን በአጽንኦት ገልጸዋል።
የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ሲአን ከሲዳማ ብልጽግና ጋር የፈጠረው ቅንጅት በምርጫ ቦርድ እውቅና እንዲያገኝ እና እነሱም የቅንጅቱ ተወካዮች ሆነው ወደ ፓርላማ እንዲገቡ የሚጠይቅ ነው። ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ቅንጅቱ ዕውን የማይሆን ከሆነ፤ ወደ ፓርላማ የሚገቡት እንደ ብልጽግና ሳይሆን “እንደ ሲአን ተወካዮች ሆነን መሆን አለበት” የሚል ነው።
የሁለቱን የፓርላማ ተመራጮች ቅድመ ሁኔታ በተመለከተ የተጠየቁት የሲዳማ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ፓርቲያቸው ስምምነት የፈጸመው ከግለሰቦች ጋር ሳይሆን ከሲአን ጋር እንደሆነ አስረድተዋል። “በብልጽግና ስም እንዲወዳደሩ ያደረገው ሲአን ስለሆነ፤ [ሲአን] ግፊት ይፈጥራል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሁለቱ የሲአን አመራሮች ወደ ፓርላማ ለመግባት ከተስማሙ፤ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሲዳማ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ ተወካዮቹን በሚልክበት የፌደራል ፓርላማ ምስረታ ላይ የመገኘት ታሪካዊ ዕድል ይገጥማቸዋል። ሁለቱ አመራሮች፤ ከዚህ ቀደምም የሲዳማ ክልል መንግስት ከተመሰረተ በኋላ በስሩ ያሉ ሁለት ቢሮዎችን የመምራት ኃላፊነት ያገኙ የመጀመሪያዎቹ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በመሆን የክልሉ ታሪክ አካል ሆነዋል።
የሲዳማ ክልል መንግስት ካቢኔን ከምስረታው ጀምሮ የተቀላቀሉት አቶ ሰላሙ፤ የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኢንዱስትሪ እና ኢንተርፕራይዞች ቢሮን ከሰኔ 2011 ጀምሮ በመምራት ላይ ይገኛሉ። ከእርሳቸው ሁለት ወር ዘግይተው በኃላፊነት የተሾሙት አቶ ደሳለኝ፤ የሲዳማ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱ የሲዳማ ክልል ተቋማት ኃላፊዎች በመደበኛ ስራቸው ቢቀጥሉም አዲሱን ፓርላማ የመቀላቀላቸው ጉዳይ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ነው። በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለተመረጡ አዲስ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ባለፈው ሳምንት በተሰጠ ስልጠና ላይም ሁለቱ የፓርላማ ተመራጮች አለመገኘታቸው ተነግሯል። በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል የተሰጠው ይኸው ስልጠና፤ የተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብን ለአዳዲስ የፓርላማ ተመራጮች ለማስተዋወቅ ያለመ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)