በሃሚድ አወል
ነገ መስከረም 20፤ 2014 በሶስት ክልሎች የሚካሄደውን ምርጫ 11 ሀገር በቀል የሲቪክ ማህበራት እንደሚታዘቡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ነገ ምርጫ የሚካሄደው፤ በሐረሪ እና በሶማሌ ክልል ባሉ ሁሉም የምርጫ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ክልል 11 ዞኖች እና ሁለት ልዩ ወረዳዎች ነው።
በምርጫ ቦርድ ፍቃድ ከተሰጣቸው 11 የሲቪክ ማህበራት መካከል አምስቱ፤ ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም ክልሎች ታዛቢዎቻቸውን እንዳሰማሩ የቦርዱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሶልያና ሽመልስ ተናግረዋል። ቀሪዎቹ ስድስቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ታዛቢዎችን ያቀረቡት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምርጫ በሚካሄድባቸው ሁሉም አካባቢዎች ታዛቢዎችን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ ድሬ የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ)፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ህብረት ለምርጫ እና የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ናቸው።
የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊዋ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 19፤ 2014 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ለነገው ምርጫ የሚሆኑ ቁሳቁሶች ስርጭት በአብዛኛው መጠናቀቁን አስረድተዋል። በሐረሪ ክልል በሁሉም ምርጫ ክልሎች እና ምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁሶች ተሰራጭቶ ለምርጫ ዝግጁ መሆኑን ሶልያና አስታውቀዋል። የቁሳቁስ ስርጭቱ፤ ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ የሐረሪ ተወላጆች በተከፈቱ 17 ምርጫ ጣቢያዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መገባደዱን ጠቁመዋል።
በደቡብ ክልል ምርጫ ከሚከናወንባቸው ምርጫ ክልሎች ውስጥ፤ ከአራቱ በስተቀር በሁሉም ቁሳቁሶች መድረሳቸውን ኃላፊዋ ገልጸዋል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ በሚካሄድባቸው የክልሉ አካባቢዎች፤ ለድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ቦርዱ አሰራጭቶ መጨረሱን ሶልያና አስታውቀዋል። በሶማሌ ክልል ከአምስት ምርጫ ክልሎች ውጪ በሌሎቹ የቁሳቁስ ስርጭቱ ከሞላ ጎደል መጠናቀቁንም አክለዋል።
የምርጫ ካርድ አጠቃቀምን በተመለከተ፤ ቦርዱ ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ በተወሰነባቸው የምርጫ ክልሎች እንደገና ምዝገባ ባለማከናወኑ፤ ሰኔ 14 ድምጽ የሰጡ መራጮች በመታወቂያቸው መምረጥ እንደሚችሉ አብራርተዋል። ድጋሚ ምርጫ የሚካሄድባቸው መስቃንና ማረቆ 2፣ ቡሌ እና ጉመር 2 የተባሉ የምርጫ ክልሎች ናቸው። በደቡብ ክልል ከሚገኙት ከእነዚህ የምርጫ ክልሎች ሁለቱ ለፓርላማ መቀመጫ ድምጽ የሚሰጥባቸው ናቸው።
ነገ ምርጫ በሚከናወንባቸው በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራ ዝግ እንዲያደርጉ ምርጫ ቦርድ አሳስቧል። ሰኔ 14፤ 2013 ምርጫ በተካሄደባቸው አካባቢዎች መስሪያ ቤቶች ዝግ እንደነበሩ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)