በሃሚድ አወል
በሶማሌ ክልል በሚገኘው ሞያሌ ምርጫ ክልል ስር፤ በአንድ ጣቢያ ያሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች ለደህነንታቸው በመስጋታቸው ምክንያት በአካባቢው የሚደረገው ምርጫ እንዲቋረጥ መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናገሩ። ቦርዱ ምርጫው እንዲቋረጥ ያደረገው ከምርጫ አስፈጻሚዎቹ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሞያሌ ምርጫ ክልል በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ድንበር ላይ እንደሚገኝ ያስታወሱት ብርቱካን፤ ቦርዱ በአካባቢው ያለውን ሁኔታ ሁለቱም ክልሎች እንዲያውቁት ማድረጉን ገልጸዋል። አጋጠመ የተባለውን የጸጥታ ስጋት ምንነት በተመለከተ ከጋዜጠኞች የተጠየቁት ሰብሳቢዋ፤ “ምርጫ አስፈጻሚዎችን እየጠበቁ ያሉት የሶማሌ ክልል ሚሊሺያዎች ናቸው። እዚያው አካባቢ የኦሮሚያ ፖሊስን በማየታቸው ግራ በመጋባት፤ ‘ደህንነት አልተሰማንም ብለው ነው ሪፖርት ያደረጉት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በሶስት ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ምርጫ በተመለከተ በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫ ነው። በተወሰኑ ቦታዎች ምርጫ እና የህዝበ ውሳኔ ድምጽ አሰጣጥ እየተደረገ ባለበት የደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን አንድ የምርጫ ታዛቢ በፖሊስ ታስሮ እንደነበር ሪፖርት እንደደረሳቸው ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል።
“ታዛቢው አሁን ተፈትቶ መታዘቡን ቀጥሏል” ያሉት ብርቱካን፤ “ይህን ተግባር የፈጸሙት አካላት በህግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን” ብለዋል። በዚሁ ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በሚገኘው የጉራ ፈርዳ ወረዳ በጸጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ አለመካሄዱን ያስታወሱት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ መራጮች በየምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እዚያው እየተመዘገቡ፤ ድምጽ እየሰጡ መሆኑንም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)