የአብኑ ጣሂር መሐመድ የአማራ ቱሪዝም ቢሮን እንዲመሩ ተሾሙ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ጣሂር መሐመድ የአማራ ክልል የቱሪዝም ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ ተሾሙ። የአማራ ክልል ምክር ቤት፤ አቶ ጣሂርን ጨምሮ 24 የክልሉ መንግስት ተቋማትን የሚመሩ ኃላፊዎችን ሹመት በዛሬው የምስረታ ጉባኤው አጽቋል። 

ምክር ቤቱ ከዚህም በተጨማሪ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተለያዩ ዘርፎችን የሚያስተባብሩ ሶስት የስራ ኃላፊዎችን ሹመትም አጽድቋል። የአማራ ክልልን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ የተሾሙት ጌታቸው ጀምበር ናቸው።      

የአማራ ክልልን በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ የተሾሙት ጌታቸው ጀምበር ናቸው

የቀድሞው የክልሉ ሰላም እና ህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪነት ሹመት አግኝተዋል። አቶ ስዩም መኮንን የማህበራዊ ጉዳዮች ክላስተርነት በአስተባባሪነት እንዲመሩ ሹመት ተሰጥቷቸዋል። 

በፌደራል የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት አይናለም ንጉሴ ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ጉዳዮች አስተባበሪ ሆነዋል። አይናለም ንጉሴ የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተሾሙት በጥቅምት 2011 ነበር። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)