የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይን ጨምሮ ሰባት የተመድ ሰራተኞች ከሀገር እንዲወጡ ታዘዙ

የኢትዮጵያ መንግስት፤ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኮድርን ጨምሮ ሰባት ለዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅት የሚሰሩ ግለሰቦች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ አንዲወጡ አዘዘ፡፡ ሰባቱ ግለሰቦች ከሀገር እንዲወጡ የታዘዙት “በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት” ተወንጅለው ነው። 

ከእነዚህ የዓለም አቀፍ ድርጅት ሰራተኞች መካከል አምስቱ፤ በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (UNOCHA) በተለያየ ኃላፊነት ቦታ የሚሰሩ ናቸው። በኢትዮጵያ የጽህፈት ቤቱ ተጠባባቂ ምክትል አስተባባሪ ሚስተር ግራንት ሊቴ፣ ተጠባባቂ ምክትል አስተባባሪዋ ሚስ ጋዳ ኢል ታሂር እና ምክትል ቢሮ ኃላፊው ሳኢድ ሞሐመድ ትዕዛዙ ከተላለፈላቸው ውስጥ ይገኙበታል።

በ72 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ አንዲወጡ ከታዘዙት የተመድ ሰባት ሰራተኞች መካከል የዩኒሴፍ የኢትዮጵያ ተወካይ አደል ኮድር ይገኙበታል | ፎቶ፦ ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ

የUNOCHA የሠላም እና ልማት አማካሪም ከሐገር እንዲወጡ ተወስኖባቸዋል። በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን (OHCHR) የኢትዮጵያ ቢሮ በቡድን መሪነት የሚሰሩ አንድ የተቋሙ ባልደረባም ተመሳሳይ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ተገልጿል።   

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሰባቱ ግለሰቦች በጻፈው ደብዳቤ ከዛሬ መስከረም 20፤ 2014 ጀምሮ ባሉት ሶስት ቀናት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቅቀው እንዲወጡ አዝዟል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግለሰቦቹ “በሀገር ውስጥ ጉዳይ ገብተዋል” ከሚል ክስ ባለፈ፤ በየትኞቹ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደገቡ ያለው ነገር የለም። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)