የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በቀጣዮቹ ቀናት ይወያያል ተባለ

በተስፋለም ወልደየስ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንደሚወያይ በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር ኒኮላ ሪቬየር ተናገሩ። በተመድ የአየርላንድ አምባሳደር ጄራልዲን ባይረን ኔሰንም በኢትዮጵያ ላይ ያተኮረው የምክር ቤቱ ውይይት “በጣም በቅርቡ” እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ሁለቱ አምባሳደሮች ይህንን የተናገሩት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሰባት የተመድ ከፍተኛ ሰራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። የጸጥታው ምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት በሊቢያ ወቅታዊ ጉዳይ  ላይ የመከሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነገ አሊያም በቀጣይ ቀናት ለውይይት ሊቀርብ ይችላል ተብሏል። 

ነገ የሚገባውን የፈረንጆቹን ጥቅምት ወር ተከትሎ የጸጥታው ምክር ቤትን በፕሬዝዳትነት የመምራት ኃላፊነት የምትረከበው የኢትዮጵያ ጎረቤት ኬንያ ነች። አስራ አምስት አባላት ያሉት የጸጥታው ምክር ቤት በጥቅምት ወር የሚወያይባቸውን አጀንዳዎች እና የሚኖሩትን ስብሰባዎች የሚያጸድቀው በነገው ዕለት እንደሆነ በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ሁኔታ አሁንም በጣሙኑ እንደሚያሳስባቸው የገለጹት አምባሳደሩ፤ እርሳቸው አባል የሆኑበት የጸጥታው ምክር ቤትም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በቀጣዮቹ ቀናት አሊያም ሳምንታት ይወያያል ብለዋል። “በቀጣዮቹ ቀናት በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ የማንወያይበት ምክንያት አይታየኝም” ሲሉ ሀገሪቱ እንደገና በምክር ቤቱ አጀንዳነት የመቅረቧን አይቀሬነት ጠቁመዋል።

የጸጥታው ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በትግራይ ጉዳይ ላይ ብቻ ለስምንት ጊዜያት ስብሰባ አካሂዷል። ምክር ቤቱ በትግራይ ያለውን ቀውስ በተመለከተ ለመጨረሻ ጊዜ ስብሰባ የተቀመጠው ባለፈው ነሐሴ ወር መጨረሻ ነው። 

በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚመክረው መጪው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ከሚመለከታቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የተመድ ሰራተኞችን ከሀገሩ እንዲወጡ መወሰኑ አንዱ እንደሚሆን ተገምቷል። ስለ ውሳኔው የተጠየቁት የፈረንሳዩም ሆነ የአየርላንዷ አምባሳደር፤ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉዳዩ ላይ ያወጡትን መግለጫ ማስተጋባት መርጠዋል። 

ጉተሬዝ የኢትዮጵያ መንግስት ሰባት የተመድ ሰራተኞችን ከሀገር እንዲወጡ መወሰኑ እንዳስደነገጣቸው ዛሬ ሐሙስ ምሽት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ሁሉም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ስራዎች የሚመሩት “በሰብዓዊነት፣ በሚዛናዊነት፣ በገለልተኝነት እና በነጻነት መርሆዎች ነው” ብለዋል። 

በኢትዮጵያ ስራቸውን እያከናወኑ ባሉ የተመድ ሰራተኞች “ሙሉ መተማመን” እንዳላቸው የገለጹት ዋና ጸሀፊው፤ ድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያንን ለመርዳት አሁንም ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ የሚመለከታቸው የተመድ ሰራተኞች፤ ስራቸውን ይቀጥሉ ዘንድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። 

በተመድ ሰራተኞች ላይ የተላለፈው ውሳኔን ሲሰሙ እንደ አንቶኒዮ ጉተሬዝ መደንገጣቸውን የተናገሩት አየርላንድ አምባሳደር ጄራልዲን ባይረን ኔሰን፤ “የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋሬጣ መፍጠሪያ ጊዜው አሁን አይደለም” ሲሉ ውሳኔውን ኮንነዋል። 

በትግራይ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ስጋት በተደጋጋሚ ማሰማታቸውን የጠቀሱት አምባሳደሯ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ውሳኔ ከተሰማ በኋላ በነበሩት ሰዓታት፤ ስለ ጉዳዩ የጸጥታው ምክር ቤት ባልደረቦቻቸውን ማነጋገራቸውን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። በንግግራቸው ወቅት እንዴት ወደፊት መራመድ እንዳለባቸው መወያየታቸውንም አንስተዋል። 

“ምክር ቤቱ አስፈላጊውን እርምጃ ሲወሰድ ማየት እንፈልጋለን” ያሉት አምባሳደር ጄራልዲን፤ “የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ከሚያከናውናቸው ስራዎች ጀርባ የምክር ቤቱ ጡንቻ እንዳለ ማየት እንፈልጋለን” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።

አየርላንድ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ አንስቶ በጉዳዩ ላይ የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሰበሰብ እና እርምጃ እንዲወስድ ተደጋጋሚ ግፊት ስታደርግ የቆየች ሀገር ናት። ሀገሪቱ በመስከረም ወር ተረክባው የነበረው የጸጥታው ምክር ቤትን በፕሬዝዳትነት የመምራት ሚና ዛሬ ሐሙስ መስከረም 20 ያበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]