በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 145 ሰዎች በታጣቂዎች መታገታቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ካማሺ ዞን ሴዳል ወረዳ 145 የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች “በጉሙዝ ታጣቂዎች” መታገታቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአካባቢውን ነዋሪዎች ዋቢ አድርጎ አስታወቀ። የወረዳው ነዋሪዎች “በጉሙዝ ታጣቂዎች” የታገቱት፤ “የታጣቂዎቹን ዓላማ አልደገፋችሁም” በሚል ምክንያት ነው ተብሏል። 

ኢሰመኮ ዛሬ አርብ መስከረም 21 ባወጣው መግለጫ “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከታገቱት ነዋሪዎች ውስጥ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን ይገኙበታል። ከታጋቾቹ መካከል ሁለት ሰዎች መገደላቸውንም የኮሚሽኑ መግለጫ ገልጿል። 

በታጣቂዎች ከታገቱት መካከል ሁለት ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል

የዛሬ ሳምንት ሐሙስ መስከረም 14 በደረሰ ጥቃት አምስት ሺህ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንና በወረዳው መስተዳድር ግቢ ተጠልለው መገኘታቸውን ጠቁሟል። ካለፈው ሳምንት እሁድ መስከረም 16 ጀምሮ ደግሞ በአካባቢው በጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ባደረገው ክትትል እንደደረሰበት ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ከትናንተ በስቲያ ጀምሮ ነዋሪዎችን ከሴዳል ወረዳ ወደ ዳለቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆመው ኢሰመኮ፤ የሴዳል ወረዳ አመራሮችና ከወረዳው የሸሹ ነዋሪዎች “በአካባቢው በቂ የጸጥታ ኃይል የለም” ማለታቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል። በሴዳል ወረዳ በሚደርሱ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን እና ከመጋቢት 2013 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ስድስት ወራት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን የአካባቢውን ነዎሪዎች ዋቢ ያደረገው የኢሰመኮ መግለጫ አብራርቷል።  

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ከመተከል ዞን ቀጥሎ ተደጋጋሚ ጥቃት ጥቃት እየደረሰ ያለው በካማሺ ዞን ነው። ታጣቂዎች በዞኑ በሚገኘው የሴዳል ወረዳ በተለይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲዘነዝሩ ቆይተዋል። ባለፈው ዓመት ሚያዚያ አጋማሽ በሴዳል ወረዳ የምትገኘውን ዲዛ ከተማ ታጣቂዎች ለቀናት ተቆጣጥረዋት እንደነበርም አይዘነጋም። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የታገቱ እና የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳስበዋል

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት፤ በፌደራል እና በክልል መንግስታት የተወሰዱ እርምጃዎች “በቂ ባለመሆናቸው የሲቪል ሰዎችን ህይወት መታደግ አልቻሉም” ሲል በመግለጫው ተችቷል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት “ሁለንተናዊ መፍትሔ የማፈላለጉ ሂደት አሁንም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ሲልም አሳስቧል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በደረሰው ጥቃት የታገቱት እና ከሴዳል ወረዳ ተፈናቅለው በዳለቲ ከተማ የሚገኙት ነዋሪዎች ለከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይጋለጡ “አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ሲሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)