ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተነሱት የባልደራስ አመራር ከፓርቲ አባልነታቸው ሊለቁ ነው

347

በተስፋለም ወልደየስ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ባለፈው ነሐሴ ወር የተሾሙት አቶ ጌታነህ ባልቻ፤ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን ተከትሎ ከፓርቲ አባልነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ። ፓርቲው የአቶ ጌታነህን ከምክትል ፕሬዝዳትነት መነሳት ቢያረጋግጥም፤ የአመራር ሽግሽጉ ግን ገና አለመጠናቀቁን አስታውቋል። 

የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት በአቶ ጌታነህ ምትክ አሁን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እየሰሩ ያሉት አቶ አምሃ ዳኘው ናቸው። አዲሱ ምክትል ፕሬዝዳንት የባልደራስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ የፓርቲው የኢኮኖሚ ጉዳይ ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። 

የፓርቲውን የምርጫ ማኒፌስቶ በማዘጋጀት ጉልህ ሚና የነበራቸው አቶ አምሃ፤ በአዲስ አበባ ምርጫ ክልል 28 ባልደራስን ወክለው ለፓርላማ መቀመጫ ተወዳድረዋል። የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ አቶ አምሃ የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታን የተረከቡት “በጊዜያዊነት” መሆኑን ገልጸዋል። የፓርቲው የአመራር ሽግሽግም ገና አለመጠናቀቁን አክለዋል። 

የባልደራስ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን በ”ጊዜያዊነት” በመስራት ላይ አቶ አምሃ ዳኘው መሆናቸውን ፓርቲው አስታውቋል

ከምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲነሱ የተደረጉት አቶ ጌታነህ፤ “ወደነበሩበት ኃላፊነታቸው ይመለሱ አሊያም ቀድሞ ይመሩት በነበረው የፖለቲካ ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊነታቸው ይቀጥሉ?” በሚለው ጥያቄ ላይ ውይይት እንዳልተደረገ እና ከውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰ ዶ/ር በቃሉ አስረድተዋል። በጉዳዩ ላይ አቶ ጌታነህን በማነጋገር ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ አቶ ጌታነህ ግን ከባልደራስ አባልነታቸው ጭምር ለመልቀቅ ለፓርቲው ጥያቄ ማቅረባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “ ‘እንደዚህ ሆኜ አልቀጥልም’ ብያለሁ። ‘በቃኝ! ልቀቁኝ እያልኩ ነው። እነርሱ ግን ‘አንቀበልም ብለዋል” ሲሉ የመልቀቂያ ጥያቄያቸው አሁን ያለበትን ደረጃ አብራርተዋል።  

ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን በመጀመሪያ የተመለከቱት እንደ ማንኛውም ሰው በፌስቡክ በተሰራጨ መረጃ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ጌታነህ፤ ከቀናት በኋላ አንድ የፓርቲው አመራር ተመሳሳዩን መልዕክት በቃል እንደነገሯቸው አስረድተዋል። እስካሁንም ድረስ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው መነሳታቸውን የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ ከፓርቲው እንዳልደረሳቸውም አመልክተዋል። 

ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተነሱት አቶ ጌታነህ ባልቻ፤ ባልደራስን ወክለው በሰኔ 2013 በተካሄደው ምርጫ ለፓርላማ ተወዳድረው ነበር

ላለፉት 16 ዓመታት በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአባልነት እና በአመራርነት ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩት አቶ ጌታነህ፤ የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተመደቡት ከአንድ ወር በፊት ነበር። አቶ ጌታነህ የፓርቲውን ሁለተኛ ትልቅ ስልጣን የተረከቡት፤ ፓርቲውን ከምስረታው ጀምሮ በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ግሩም ሀብቴ ከኃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።

ከባልደራስ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታነህ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተመደቡትም ሆነ ከስልጣናቸው የተነሱት፤ አሁን በእስር ላይ በሚገኙት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ውሳኔ እንደሆነ የፓርቲው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በባልደራስ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ተጠሪነቱ ለፕሬዝዳንቱ ሲሆን፤ የሚመረጠውም በፕሬዝዳንቱ አቅራቢነት ነው።

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ፕሬዝዳንቱ በማይኖርበት ጊዜ እርሱን ተክቶ የመስራት ስልጣን በመተዳደሪያ ደንቡ ተሰጥቶታል። ከፕሬዝዳንቱ በዝርዝር የሚሰጡትን ስራዎች እንደሚያከናውንም በደንቡ ተቀምጧል። ደንቡ ለፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ኃላፊነት የመስጠት፣ የመከታተል እና የመቆጣጠር ስልጣንን ለፕሬዝዳንቱ ይሰጣል። 

የባልደራስ የስራ አስፈጻሚ አባላት ፓርቲውን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው ከተገኙ፤ የሥነ-ሥርዓት ክስ እስከሚመሰረትባቸው ድረስ የማገድ ስልጣን የተሰጠው ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው 

የመተዳደሪያ ደንቡ፤ የፓርቲው አባላት የሥነ-ሥርዓት (ዲሲፕሊን) ጥፋቶችን ፈጽመው በሚገኙበት ወቅት የሚወሰዱ ቅጣቶችን እና የውሳኔ አሰጣጦችንም በዝርዝር ደንግጓል። የባልደራስ የስራ አስፈጻሚ አባላት ፓርቲውን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው ከተገኙ፤ የሥነ-ሥርዓት ክስ እስከሚመሰረትባቸው ድረስ የማገድ ስልጣን የተሰጠው ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው። 

ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ የሚደረገው እገዳ የሚጸድቀው የኮሚቴውን 2/3ኛ ድምጽ ሲያገኝ እንደሆነም በደንቡ ላይ ተብራርቷል። እንደ ፓርቲው ምንጮች ገለጻ፤ አቶ ጌታነህ ከስልጣናቸው የተነሱበት አካሄድ የፓርቲውን የመተዳደሪያ ድንጋጌዎች ያልተከተሉ ናቸው። 

ይህን ውንጀላ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ ጉዳዩ “በሂደት ላይ ያለ እና ያላለቀ ጉዳይ በመሆኑ” ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተነሱበት ምክንያት በተመለከተም “ይህ የፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

ውንጀላውን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ፤ ጉዳዩ “በሂደት ላይ ያለ እና ያላለቀ ጉዳይ በመሆኑ” ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል

የባልደራስ ፓርቲ ምንጮች ግን አመራሩ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉት በኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ ካደረጉት ንግግር ጋር በተያያዘ ነው ይላሉ። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት አቶ ጌታነህ የምክንያቱን እውነታን አረጋግጠዋል። ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው ለመነሳታቸው በምክንያትነት ከቀረቡላቸው ጉዳዮች አንዱ “በኢዜማ ጉባኤ ላይ ለምን ተገኘህ?” የሚል እንደነበር ተናግረዋል። “በጉባኤው ላይ ‘አብረን እንስራ’ ብለህ ተናግረሃል” የሚለው ሌላው ምክንያት እንደሆነም ያስረዳሉ። 

ኢዜማ የዛሬ ሁለት ሳምንት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ባልደራስን ጨምሮ የሌሎች ፓርቲዎች ተወካዮች በክብር እንግድነት እንዲገኙ በደብዳቤ ግብዣ አቅርቦ ነበር። በዚሁ መሰረት አቶ ጌታነህ ባልቻ ባልደራስን ወክለው በጉባኤው መዝጊያ ላይ ተገኝተዋል። የእናት ፓርቲ ዋና ጸሀፊ አቶ ጌትነት ወርቁ ሌላው በስፍራው የተገኙ የተቃዋሚ ፖርቲ አመራር ናቸው። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የአቶ ጌታነህ የተቀረጸ የስምንት ደቂቃ ንግግር ላይ በእርግጥም የአብሮ መስራት ጥያቄ በተደጋጋሚ ተነስቷል። “በሚያስማሙን፣ በምንወያይባቸው ጉዳዮች ላይ መስራት አለብን” ሲሉ የሚደመጡት የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት፤ ሀገርን ለማሳደግ፣ ልማትን ለማፋጠን እና ከድህነት ለማውጣት በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። 

በኢዜማ ጠቅላላ ጉባኤ የመስጊያ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ጌታነህ ባልቻ፤ “በየትኛውም ጉዳዮች ላይ ለመስራት እኛ እንደ ባልደራስ ፍቃደኞች ነን” ሲሉ ተደምጠዋል

ሆኖም ያንን ማድረግ የሚቻለው በፓርቲዎች መካከል “የሀሳብ ፍጭት ሲኖር” እንደሆነ እርሳቸውም ሆነ ፓርቲያቸው እንደሚያምኑ ለጉባኤው ተሳታፊዎች አስረድተዋል። “ሀገራችን ላይ ዲሞክራሲ ለማስፈን እንድንችል የሚረዳን እና የሚያስመቸን ሁኔታ መፍጠር የምንችለው፤ የተለያየ ሀሳብ እያመጣን፣ እያፋጨናቸው ስንሄድ ነው። ይሄ ሀሳብ እየገፋ መሄድ አለበት” ሲሉ አቶ ጌታነህ ለኢዜማ አባላት ተናግረዋል። 

“በየትኛውም ጉዳዮች ላይ ለመስራት እኛ እንደ ባልደራስ ፍቃደኞች ነን። ሁሌም ከሁሉም ጋር እንሞካክራለን። ደጋግመን አብረን መስራት አለብን እንላለን” ሲሉ ለጉባኤው ታዳሚ የፓርቲያቸውን አቋም አሳውቀው ነበር። 

በጉባኤው ማግስት ይህ የእርሳቸው ንግግር የተወሰኑ የባልደራስ አባላትን ቅር ማሰኘቱን እንደሰሙ የሚናገሩት አቶ ጌታነህ፤ በጉዳዩ ላይ ተገቢውን ማብራሪያ ለመስጠት እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው መነሳታቸው እንደተነገራቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከኃላፊነታቸው የተነሱበት አካሄድ “የፓርቲውን ደንብ የጣሰ ነው” የሚል ቅሬታ ያላቸው አቶ ጌታነህ፤ ከፓርቲው ጭምር ለመሰናበት ጥያቄ አቅርበው ምላሹን በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።፡   

የባልደራስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሹም ሽርን ተከትሎ በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሽምግልና ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ የፓርቲው ምንጮች አስታውቀዋል። የሽምግልና ንግግሮችን እያከናወነ ያለው የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ አባላት የተካተቱበት እና አምስት አባላት ያሉት ቡድን እንደሆነም ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)