በኢትዮጵያ ሊደረግ የታቀደው ብሔራዊ ውይይት፤ የታጠቁ ቡድኖችን ጭምር ሊያካትት እንደሚገባ ኦፌኮ አሳሰበ

273

በተስፋለም ወልደየስ

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በኢትዮጵያ ሊደረግ የታቀደው ብሔራዊ ውይይት የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖችን ሊያካትት ይገባል አለ። ፓርቲው “የፖለቲካ እስረኞች” በሚል የጠራቸው ግለሰቦችም ከእስር ተፈትተው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ መፈቀድ እንዳለበት አሳስቧል። 

ኦፌኮ ይህን ያለው ብሔራዊ ውይይትን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 15፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። በኢትዮጵያ “ስር የሰደደ እና ከምንጊዜውም በላይ እየተባባሰ የመጣ የፖለቲካ ቀውስ” መኖሩን በመግለጫው የጠቆመው ኦፌኮ፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ሊፈታ የሚችለው “በሐቀኛ፣ እውነተኛ እና ሁሉን ያካተተ ብሔራዊ ውይይት ብቻ” መሆኑን ገልጿል። 

ተቃዋሚ ፓርቲው በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት የሚያግዝ “ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት” እንዲደረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲጠየቅ ቢቆይም፤ ለውይይት እና የድርድር ጥሪዎቹ ከገዢው ፓርቲ በኩል ቀና ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱን አስታውሷል። ገዢው ፓርቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለብሔራዊ ውይይት አስፈላጊነት መናገር መጀመሩን ብዙዎች “በጣም ዘግይቷል” ብለው ቢያጣጥሉትም፤ በኦፌኮ በኩል ግን “ውይይቱ ሙሉ ለሙሉ ከሚቀር ዘግይቶም ቢሆን ቢካሄድ ይመረጣል” የሚል አቋም እንዳለ በመግለጫው ተጠቅሷል። 

ሊካሄድ የታሰበው ብሔራዊ ውይይት “በትክክል እና በእውነት ተመርቶ፤ ኢትዮጵያን ከውድቀት መታደግ አለበት” የሚል ጠንካራ አቋሙን በመግለጫው ያንጸባረቀው ኦፌኮ፤ ለዚህም አራት “ቅድመ ሁኔታዎች” መሟላት እንዳለባቸው አስገንዝቧል። ፓርቲው በመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታነት ያስቀመጠው በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም እና ተፈላሚ ወገኖች ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ ውይይት እንዲያደርጉ ነው።

ኦፌኮ በሁለተኛነት ያነሳው ጉዳይ ውይይቱ የሚመራበት አካሄድ የተመለከተ ነው። “ብሔራዊ ውይይቱ በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ባለው፤ ገለልተኛ፣ ተዓማኒ እና የማያዳላ አካል መመራት ይኖርበታል” ሲል ቅድመ ሁኔታውን ያስቀመጠው ኦፌኮ፤ አሁን ባለው ወቅታዊ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ የተነሳ ይህን የሚያሟላ አካል በሀገር ውስጥ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ጠቁሟል። ውይይቱን የሚመራው አካል፤ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ እውቅና እና ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚገባም ፓርቲው በተጨማሪነት አስገንዝቧል። 

በተቃዋሚ ፓርቲው በኩል በሶስተኛነት የቀረበው ቅድመ ሁኔታ ብሔራዊ ውይይቱ “ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች ያካተተ መሆን አለበት” የሚለው ነው። ኦፌኮ በዚህ ቅድመ ሁኔታው ላይ “የታጠቁ ተቃዋሚ ቡድኖች ጭምር መካተት አለባቸው” ቢልም በስም ከመዘርዝር ግን ተቆጥቧል። ሆኖም ሁሉም ቡድኖች በውይይቱ ይሳተፉ ዘንድ ለማስቻል፤ “ሕጋዊ እና የደህንነት መሰናክሎች መወገድ” እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።

ብሔራዊ ውይይት ከመደረጉ አስቀድሞ መፈጸም ይኖርባቸዋል በሚል በኦፌኮ ከቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎች በመጨረሻነት የተጠቀሰው በፖለቲካ ምክንያት በእስር ላይ ይገኛሉ የተባሉ እስረኞች ፍቺ ጉዳይ ነው። “የፖለቲካ እስረኞች” በሚል በኦፌኮ መግለጫ በደፈናው የተጠቀሱ ግለሰቦች በሙሉ ከእስር ተፈትተው በብሔራዊ ውይይቱ ላይ እንዲሳተፉ መፈቀድ እንዳለበትም በቅደም ሁኔታው ላይ ተቀምጧል።

ኦፌኮ፤ የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በአዲስ አበባ ከተቀሰቀሰው ሁከት ጋር በተያያዘ በርካታ አመራሮቹ እና አባላቱ ታስረውበታል። በእስር ላይ ካሉት የፓርቲው ተጠቃሽ ሰዎች መካከል ምክትል ሊቀመንበሩ በቀለ ገርባ፣ የአመራር አባሉ አቶ ደጀኔ ጣፋ እና የፓርቲው አባል ጃዋር መሐመድ ይገኙበታል።

“የታቀደው ብሔራዊ ውይይት ሂደቱ እነዚህን አነስተኛ መመዘኛዎች እስካልጠበቀ ድረስ እና የብሔራዊ ውይይቱ ሂደት በእውነተኛ መንገድ ሐቅን ያልተከተለ ከሆነ የእኛ ተሳትፎ ትርጉም የለሽ፤ አጠቃላይ ሂደቱም ከንቱ እንደሚሆን ከወዲሁ እናሳስባለን” ያለው ኦፌኮ፤ ለዚህ ጥረቱም መላው ኢትዮጵያውያን እና ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን። 

በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚስተዋሉ ስር የሰደዱ ችግሮች “ዘለግ ያለ መፍትሔ ለማበጀት” ያለመ ነው የተባለለት ብሔራዊ የምክክር መድረክ፤ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ አስተባባሪዎቹ ከአንድ ወር በፊት አስታውቀው ነበር። በምክክሩ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ 22 ባለድርሻ አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በወቅቱ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)