የደቡብ ክልል ምክር ቤት፤ ለአዲሱ 11ኛ ክልል የስልጣን ርክክብ ለማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

• የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቅዳሜ በሚያካሂደው ስብሰባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔ ውጤትን ያጸድቃል

በተስፋለም ወልደየስ

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የስልጣን ርክክብ ለማድረግ ለሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ጥቅምት 22፤ 2014 አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ። ከዚህ ስብሰባ አንድ ቀን አስቀድሞ አስቸኳይ ስብሰባውን የሚያካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን ለመመስረት የተካሄደውን የህዝበ ውሳኔ ውጤት ያጸድቃል ተብሏል።

በደቡብ ክልል ስር የነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ የራሳቸውን የጋራ ክልል ለመመሰረት የሚያስችላቸውን ህዝበ ውሳኔ ያካሄዱት ባለፈው መስከረም 20፤ 2014 ነበር። በዕለቱ ድምጽ ለመስጠት ከወጡ 1,262,679 የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል 96 በመቶው የአዲሱን ክልል መመስረት መደገፋቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። 

በህዝበ ውሳኔው መሰረት ከደቡብ ክልል ወጥተው የራሳቸውን ክልል የመመሰረት ይሁንታ ያገኙት የካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው። የአምስቱን ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ተቀብሎ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ ያቀረበው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።

ከደቡብ ክልል ወጥተው የራሳቸውን ክልል የመመሰረት ይሁንታ ያገኙት የካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ እና ምዕራብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ናቸው | ፎቶ፦ የካፋ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

ምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ለፌደሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ እንዳሳወቀ የምክር ቤቱ ህዝብ ግንኙነትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ምክር ቤቱ በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 20፤ 2014 በሚያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል። በዕለቱ ምክር ቤቱ ሌሎች አጀንዳዎችን እንደሚመለከትም ጨምረው ገልጸዋል። 

ከዚህ ስብሰባ አንድ ቀን በኋላ በሚደረገው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 11ኛው ክልል መሆኑ የሚረጋገጥበት ይሆናል ተብሏል። በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ ክልል የስልጣን የሚያስረክብ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሰረት በሕዝበ ውሳኔ የሚፈጠር እና ከክልል ምክር ቤት ስልጣን የሚረከብ አዲስ ክልል፤ ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባል ይሆናል።  

“አካሄዱ በህገ መንግስቱ መሰረት ተፈጻሚ መሆን ስላለበት፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ደግሞ የስልጣን ርክክብ ያደርጋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የስልጣን ርክክብ ያደርጋል ወይም ደግሞ ክልል ሆኖ መውጣቱን ያሳውቃል ማለት ነው” ሲሉ አቶ ተረፈ ሂደቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

ከደቡብ ክልል በመውጣት የራሱን ክልል በመመስረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመጀመሪያው አይደለም። በክልሉ ስር የነበረው የሲዳማ ዞን፤ በህዳር 2012 በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ራሱን ችሎ ክልል ሆኖ ለመደራጀት የሚያስችለውን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘቱ፤ የኢትዮጵያ 10ኛ ክልል መሆኑ እውን ሆኗል።

የያኔው የሲዳማ ዞን አስተዳደር ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ስልጣኑን የተረከበው ህዝበ ውሳኔው በተካሄደ በሰባተኛ ወሩ ነበር። በመጪው ሰኞ ጥቅምት 22 ከደቡብ ክልል ጋር በይፋ የሚለያዩት አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ፤ የአዲሱን ክልል የማስተዳደር ስልጣን የሚረከቡት ህዝበ ውሳኔ ባካሄዱ በአንደኛ ወራቸው ይሆናል። የአዲሱ ክልል ምስረታ ይፋ የሚደረግበት ስነ ስርዓትም፤ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሊካሄድ እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የአዲሱ ክልል መስራቾች በደቡብ ክልል ምክር ቤት ውስጥ 52 ተወካዮች አሏቸው። ተወካዮቹ ወደፊት የሚመሰረተውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤትን ሲቀላቀሉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ወደ 239 ይቀንሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)