በእስር ላይ በምትገኘው የአሐዱ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በተስፋለም ወልደየስ

ካለፈው አርብ ጀምሮ በእስር ላይ በምትገኘው የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጋዜጠኛ ሉዋም አትክልቲ ላይ የስምንት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ። ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን ዛሬ የፈቀደው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው።

በጋዜጠኛዋ ላይ የተከፈተውን የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የሚመለከተው ችሎት ለዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 18፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ የተጠርጣሪዋን ምርመራን እያከናወነ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የደረሰበትን ግኝት ለመስማት ነበር። በዛሬው የችሎት ውሎ ስለ ምርመራ ግኝቱ በፍርድ ቤት የተጠየቀው ፖሊስ፤ ባለፉት አምስት ቀናት “አከናውኛቸዋለሁ” ያላቸውን ተግባራት ማስረዳቱን የጋዜጠኛዋ ጠበቃ አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዋን በሚመለከት ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ለኢትዮ ቴሌኮም ደብዳቤ መጻፉን በመጥቀስ፤ ከሁለቱ ተቋማት ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ መናገሩን ጠበቃው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተፈቀደለት የምርመራ ቀናት፤ የጋዜጠኛ ሉዋም “ግብረ አበር ነው” ያለውን አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ለችሎቱ ማስረዳቱን አቶ ጥጋቡ አክለዋል።

ይህን ተከትሎም መርማሪ ፖሊስ፤ የሁለቱን የመንግስት ተቋማት ምላሽ ለመቀበል እና ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ጋዜጠኛ ሉዋምን በመወከል ዛሬ በችሎት የተገኙት አቶ ጥጋቡ እና ሌላኛው ጠበቃ አቶ አበባው አበበ  በፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ጥያቄ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ሁለታችንም ተራ በተራ ዕድል ተሰጥቶን ተናግረናል። አንደኛ ያልነው፤ ብሔራዊ ደህንነት እና ኢትዮ ቴሌኮም ትልቅ ተቋማት ናቸው። የሀገር ህልውናን የሚያስጠብቁ፣ መረጃ የሚጠብቁ ስለሆኑ ግለሰቧ በዋስትና ብትወጣ ከተቋማቱ ጋር በመገናኘት የምትፈጥረው ችግር የሌለ መሆኑን ነው” ሲሉ የመጀመሪያ መከራከሪያቸው ምን እንደነበር አቶ ጥጋቡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ጋዜጠኛዋ በዋስትና ብትወጣ “ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ያላት፣ የስራ ቦታዋ የሚታወቅ፣ ፖሊስ በቀን ሁለት ሶስት ጊዜ ቢደውላላት መቅረብ የምትችል መሆኑን” በመጥቀስ የዋስትና መብቷ እንዲፈቀድ ጠበቆቹ ለችሎቱ ማመልከታቸውን አቶ ጥጋቡ ገልጸዋል። ፖሊስ ጋዜጠኛዋን “ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር በመገናኘት ጠርጥሬያታለሁ” በሚል በቁጥጥር ስር እንዳዋላት ለፍርድ ቤቱ ያነሱት ጠበቆቹ፣ በዚህ ጉዳይ ላይም ቢሆን “ፖሊስ በፍጹም መረጃ እንደማያገኝ እና ጋዜጠኛዋ ሙያዋን አክብራ የምትሰራ፣ ኃላፊነት የሚሰማት መሆኗን” ማብራራታቸውን አቶ ጥጋቡ ጨምረው ገልጸዋል።

የጠበቆቹን መከራከሪያ ያደመጠው ፖሊስ ጋዜጠኛ ሉዋም “የተሳሳተ ዜና በመስራት መንግስት እና ህዝብን አሸብራለች” በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲሆን ጠይቋል ብለዋል። ጋዜጠኛዋን ለእስር ያበቃው ዜና በደቡብ ወሎ የምትገኘው ሐይቅ ከተማ በሕወሓት ቁጥጥር ስር መዋሏን የሚገልጽ ነበር። በአካባቢው የሚገኙ አንድ ባለስልጣን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በመመስረት የተዘጋጀው ይሄ ዜና ባለፈው ሳምንት አርብ ጥቅምት 12፤ 2014 በአሃዱ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ የሶስት ሰዓት የዜና እወጃ ተላልፏል።

ዜናው ከተላለፈ በኋላ የተቀየሩ ሁነቶች ይኖሩ እንደሁ በማለት የራዲዮ ጣቢያው ጋዜጠኞች ባደረጉት ማጣራት እና የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ጥቆማ፤ የተላለፈው ዜና የተሳሳተ እንደነበር እንደተደረሰበት ከጣቢያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል። የራዲዮ ጣቢያው ከሐይቅ ከንቲባ በስልክ ያገኘውን መረጃ በማካተት፤ በዚያኑ ዕለት ቀን ስድስት ሰዓት ላይ በተላለፈ የዜና እወጃው እርማት ማድረጉን እና ይቅርታ መጠየቁ ተገልጿል።

ዜናውን ያዘጋጀችው ጋዜጠኛ ሉዋም አታክልቲ እና የዕለቱ የዜና አርታኢ የነበረው ክብሮም ወርቁ ከስራቸው ታግደው እንደነበር የጣቢያው ምንጮች አስረድተዋል

የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ የጣቢያው የኤዲቶሪያል ኮሚቴ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ እስኪያስተላልፍ ድረስ፤ ዜናውን ያዘጋጀችው ጋዜጠኛ ሉዋም እና የዕለቱ የዜና አርታኢ የነበረው ክብሮም ወርቁ ከስራቸው ታግደው እንደነበር የጣቢያው ምንጮች አስረድተዋል። ጉዳዩን የተመለከተው የኤዲቶሪያል ኮሚቴ “ዘገባው ስህተት መሆኑን ጣቢያው አምኖ ይቅርታ በመጠየቁ ጋዜጠኞቹ ከስራቸው ታግደው መቆየት አይገባቸውም” በሚል ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ እግዱን ማንሳቱን ምንጮች አክለዋል።

የአሐዱ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያን ከወራት በፊት የተቀላቀለችው ጋዜጠኛ ሉዋም፤ የስራ እግዱ ከመነሳቱ በፊት ባለፈው አርብ ጥቅምት 12 አስር ሰዓት ገደማ ከቢሮዋ ስትወጣ በቁጥጥር ስር መዋሏን የጣቢያው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገረው ጋዜጠኛዋን የያዛት “የተሳሳተ ዘገባ ሰርታለች” በሚል ከሆነ፤ ጉዳዩ የፍትሐ ብሔር ስለሆነ፣ በእስር መቆየት ሳይገባት፣ በዋስትና እንድትለቀቅ ጠበቆቿ በዛሬው ችሎት ላይ ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠበቃ ጥጋቡ ተናግረዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት በመቀነስ ስምንት ቀናት ብቻ ፈቅዷል። በዚህም መሰረት ችሎቱ የምርመራው ሂደት የደረሰበትን ደረጃ ለማድመጥ ለሚቀጥለው ሳምንት አርብ ለጥቅምት 26፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬ ውሎውን አጠናቅቋል።

በተመሳሳይ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ የተከፈተው የጋዜጠኛ ክብሮም ቀጣይ ቀጠሮም ጥቅምት 26 እንደሆነ አቶ ጥጋቡ ገልጸዋል። በዛሬው የችሎት ውሎ የሉዋም “ግብረ አበር ነው” በሚል በፖሊስ የተጠቀሰው የጋዜጠኛ ክብሮም ጉዳይ ተነስቶ እንደነበርም ጠቁመዋል።   ፖሊስ “ግብረ አበር አድኜ ይዤያለሁ” ሲል ለፍርድ ቤት እንደገለጸው ሳይሆን፤ ክብሮም እና ሸምሲያ አወል የተባለች ሌላ ባልደረባው “ራሳቸው ህግ አክብረው የቀረቡ መሆኑን” ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ጠበቃው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረቦች ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ወደ አሐዱ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ከሄዱ በኋላ ለክብሮም እና ሸምሲያ ስልክ እንደደወሉላቸው የሚጠቅሱት ጠበቃው፤ የስልክ ጥሪውን ተከትሎ ጋዜጠኞቹ ወደ ቢሯቸው በሄዱበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አብራርተዋል። ጋዜጠኞቹ በተለምዶ ሶስተኛ ተብሎ ወደሚታወቀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና ጽህፈት ቤት መወሰዳቸውንም ጠቅሰዋል።

ጋዜጠኛ ሸምሲያ በኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ለአራት ሰዓታት ያህል ከቆየች በኋላ “ስንፈልግሽ እንጠራሻለን” በሚል መለቀቋን እና ክብሮምን ግን እዚያው እንዳቆዩት ተናግረዋል። ክብሮም በትላንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ፤ ፖሊስ ለሚያከናውነው ምርመራ ዘጠኝ ቀናት እንደተፈደለት ጠቁመዋል። ፖሊስ ጋዜጠኛውን የጠረጠረው “ከጸረ- ሰላም ሃይሎች ተልዕኮ በመቀበል፤ ለተልዕኮ አፈጻጸም የሚረዱ ወጣቶችን በመመልመል እንቅስቃሴ አድርጓል” በሚል መሆኑን አቶ ጥጋቡ አስረድተዋል።

ሉዋም አታክልቲ እና ክብሮም ወርቁ መታሰራቸው ከተረጋገጠ በኋላ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር “በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት ጋዜጠኞች በተቻለ መጠን በፍጥነት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ የህግ ድጋፍ የማግኘት  መብታቸው እንዲጠበቅ፤ እንዲሁም የመጎብኘት መብታቸው እንዲከበር እንዲያደርግ” በትላንትው ዕለት ባወጣው መግለጫ ጠይቆ ነበር። የጋዜጠኞቹን ጉዳይ እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው ማህበሩ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥራቸውን በአገሪቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ያለ ሥጋት እና ያለፍርሃት መሥራት እንዳለባቸው” ገልጿል።  

የጋዜጠኞቹ እስር “እጅግ አሳስቦኛል” ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝ ዛሬ ሐሙስ ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ በይፋዊ የፌስቡክ እና የትዊተር ገፆቹ በኩል ባሰራጨው አጭር መግለጫ “ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት እንግልት ሊገጥማቸው፤ ከብዙኃን መገናኛዎች ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የሚባሉ ጥፋቶችም ለእስር ምክንያት ሊሆኑ አይገባም” ብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)