በሃሚድ አወል
አውሎ ሚዲያ ከዛሬ ጀምሮ ሰራተኞቹን አሰናብቶ ስራ ማቆሙን ዋና አዘጋጁ በቃሉ አላምረው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ፡፡ ብዙሃን መገናኛው ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 18 ምሽት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳለው ስራውን ለማቆም የተገደደው “በመንግስት በተፈጠረ ችግር ምክንያት” ነው።
የፌደራል ፖሊስ ከአምስት ወር በፊት የድርጅቱን ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት የድርጅቱ ንብረቶች ለምርመራ ተብለው መወሰዳቸውን የገለጹት አቶ በቃሉ፤ ድርጅቱ እስካሁንም የተያዙ ንብረቶቹን ማስመለስ አለመቻሉን አስረድተዋል። በዚያን ጊዜ የታሸገው በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኒያለም ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ እስከዛሬ ድረስ አለመከፈቱን የጠቀሱት ዋና አዘጋጁ፤ በሁለቱ ምክንያቶች የተነሳ ሙሉ ለሙሉ ስራ ለማቆም መወሰኑን አብራርተዋል።

የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች በፌደራል ፖሊስ የተያዙት ባለፈው ዓመት ሰኔ 23፤ 2013 ነበር። በስራ ገበታቸው ላይ ባሉበት ወቅት የተያዙት አስራ አንዱ የአውሎ ሚዲያ ሰራተኞች፤ በተመሳሳይ ወቅት በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኢትዮ ፎረም ጋዜጠኞች ጋር በአንድ ላይ በመሆን፤ ወደ አፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ መወሰዳቸው ይታወሳል። በከተማይቱ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ታስረው የቆዩት የብዙሃን መገናኛው ሰራተኞች ከእስር የተለቀቁት ባለፈው ነሐሴ ወር ውስጥ ነበር።
የብዙሃን መገናኛው “ወደ ስራ እንዲመለስ በፍርድ ቤት ተወስኖ ነበር” የሚሉት አቶ በቃሉ፤ “የፌደራል ፖሊስ የወሰደውን ንብረት ሊመልስ አልቻለም። ያሸገውን ቢሮም ሊከፍት አልቻለም” ብለዋል። የድርጅቱን ንብረት ለማስመለስ ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም “አልተወሰነም” የሚል ምላሽ ሲሰጣቸው መቆየቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

አቶ በቃሉ “የመንግስት ደጋፊዎች” ሲሉ በሚጠሯቸው አክቲቪስቶች ተፈጽሟል የሚሉት “የስም ማጥፋት” ዘመቻ፤ ብዙሃን መገናኛውን ስራውን እንዲያቆም ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። “ ‘አሸባሪ ከተባሉ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው’ በሚል ከፍተኛ የስም ማጥፋት ተፈጽሞብናል። ከዚህ በኋላ ልንሰራ የምንችለውን ስራ ራሱ ተዓማኒነቱን ያጎድለዋል” ሲሉ በድርጊቱ ጋዜጠኞቹም ጭምር ሰለባ መሆናቸውን አስረድተዋል።
“ሚዲያውን ሊያሰራው የሚችል environment የለም። መንግስትም [ሚዲያው] እንዲዘጋ ይፈልጋል” የሚሉት ዋና አዘጋጁ፤ “በጣም አደገኛ አካሄድ ነው ያለው” ሲሉ ስላሉበት ሁኔታ አሳሳቢነት አጽንኦት ይሰጣሉ። ከነሐሴ 2011 ጀምሮ ዜናዎችን እና ፕሮግራሞችን ሲያቀርብ የቆየው አውሎ ሚዲያ ሴንተር፤ በአዲሱ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ተመዝግቦ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እውቅና ያገኘው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ነበር፡፡
ድርጅቱ ያጋጠመውን ችግር በተመለከተ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንን ለማነጋገር ጥረት አድርገው እንደው የተጠየቁት አቶ በቃሉ፤ “በተደጋጋሚ ለማነጋገር ሞክረን ምንም መልስ አልተሰጠንም” ብለዋል። ለድርጅቱ መዘጋት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስተዋጽኦ አለበት የሚል እምነታቸውንም ገልጸዋል። ስለ ጉዳዩ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)