ኮምቦልቻ – የውጊያ ዳፋ እና ሥጋት የበረታባት ከተማ

ከደሴ በስተደቡብ 25 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቀው የኮምቦልቻ ከተማ፤ በመጪው ረቡዕ አንድ አመት የሚሞላው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላፈናቀላቸው በሺህዎች ለሚቆጠሩ የሰሜን እና የደቡብ ወሎ ሰዎች መጠለያ ሆናለች። ከተፈናቃዮቹ መካከል አቅማቸው የፈቀደ ቤት ተከራይተዋል፤ ወዳጅ ዘመድ ያላቸው መጠጊያ አግኝተዋል፤ ያልሆነላቸው በርከት ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ጎዳና ወድቀዋል።

በጥቅምት መጀመሪያ ወደ ኮምቦልቻ ከተማ ብቅ ያለው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ሃሚድ አወል፤ በወሎ እየተካሄደ ያለው ውጊያ የፈጠረውን ምስቅልቅል ታዝቧል። በተሽከርካሪዎች እና ተፈናቃዮች የተጨናነቀችው ከተማ ያለፉትን ሶስት ወራት እንዴት እንዳሳለፈችም ከነዋሪዎቿ እና ከእንግዶቿ አድምጧል። በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ያሉበትን አስቸጋሪ ህይወትም ተመልክቷል።


ወቅቱ የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ነው። አዲስ ዓመት ከባተ 35 ቀናት ብቻ ያለፉ ቢሆንም፤ በደቡብ ወሎዋ የኮምቦልቻ ከተማ ግን የበዓልም ሆነ የመዝናናት ስሜት ሽታው እንኳን የለም። ለወትሮው በኮምቦልቻ ባሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ሞቅ ደመቅ ይል የነበረው የመውሊድ በዓልም፤ በዚያኑ ሰሞን የተከበረው በፈዘዘ እና በቀዘቀዘ ሁኔታ ነበር። የጨፍጋጋው ድባብ መንስኤ ከጦርነት ጋር በተያያዘ በከተማይቱ ያረበበው ስጋት ነው። 

በኮምቦልቻ ከተማ የሚነፍሰው የስጋት ንፋስ ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን፤ ወደ ከተማይቱ እግር ጥሎት ለመጣ እንግዳ ያስታውቃል። የኮምቦልቻ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ግቢን የሚጎራበተው የከተማይቱ መግቢያ ላይ ባልተለመደ መልኩ በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎች ተደርድረዋል። ሸራ የለበሱት የጭነት ተሽከርካሪዎች የተባበሩት መንግስታትድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) መለያን በየበሮቻቸው ላይ ለጥፈዋል። 

ፊታቸውን ወደ ፒያሳ አቅጣጫ አድርገው ከመንገድ ዳር በሰልፍ ከቆሙት ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች አቅራቢያ፤ ወደ ከተማይቱ የሚገቡ በርካታ መኪናዎችም በተመሳሳይ መልኩ ተደርድረው ይታያሉ። በመግቢያ ኬላው ላይ የተሰለፉት እነዚህ ተሽከርካሪዎች በጥብቅ ከተፈተሹ በኋላ ነው ወደ ከተማይቱ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው። ፍተሻው በአብዛኛው የሚከናወነው ብርቱካንማ ሰደርያ በለበሱ የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ቢሆንም የአማራ ልዩ ኃይል እና የኮምቦልቻ ከተማ ፖሊሶች የጸጥታ ቁጥጥር ስራውን በንቃት ሲያከናውኑ ይታያሉ። 

ይህን አልፈው ወደ ኮምቦልቻ የዘለቁ አሽከርካሪዎች ከዚህ ቀደም እንደነበረው በጥቂት ደቂቃዎች ከተማይቱ እምብርት መድረስ አይቻላቸውም። ቀድሞ ባለ ሶስት እግር ታክሲዎች (ባጃጅ) እና የጭነት ተሽከርካሪዎች እንደልባቸው ይመላለሱበት የነበረው ብቸኛ አውራ ጎዳና ለቁጥር በሚያዳግቱ ባጃጆች በመጨናነቁ በዝግታ መጓዝ ግድ ብሏቸዋል።

በኮምቦልቻ ለሚታየው የትራፊክ መጨናነቅ ዋነኛ ምክንያቶቹ ባጃጆች ናቸው። በከተማይቱ ያለው የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበው፤ በርካታ ባጃጆች ጦርነት ከነበረባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ወደ ኮምቦልቻ ከገቡ በኋላ ነው። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ትራንስፖርት ልማት ቡድን ተወካይ አቶ ሽመልስ አህመድ እንደሚሉት፤ ከሰሜን ወሎ ዞን ወረዳዎች ወደ ኮምቦልቻ የገቡ ባጃጆች ብዛት ከአንድ ሺህ በላይ ይሆናል። 

ከተማይቱን መተንፈሻ  ካሳጧት ባጃጆች በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት እና የአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም የሚሊሺያ አባላትን የጫኑ ተሸከርካሪዎች ከተማይቱን አቋርጠው ያልፋሉ። የመከላከያ ታርጋ የለጠፉ፣ ጭቃ የተቀቡ የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎችን ያሳፈሩ የህዝብ ማመላለሻ እና የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎችም በየቦታው ይታያሉ።

በተሽከርካሪዎች ብዛት ሳቢያ የተፈጠረው የትራፊክ መጨናነቅ፤ የከተማይቱ ነዋሪዎች በተሳፈሩበት መኪና ውስጥ እንዳሉ በርካታ ደቂቃዎች እንዲያባክኑ ይገደዳሉ። በእግር ከ15 እስከ 20 ደቂቃ ይፈጅ የነበረው መንገድ፤ በትራንስፖርት ከ30 እስከ 40 ደቂቃ መውሰድ ከጀመረ ወራትን አስቆጠሯል። የከተማይቱ መንገዶች መዘጋጋት፤ በጦርነት ግዳጅ ላይ ያሉ የመከላከያ መኪኖችን እና አምቡላንሶችን ጭምር በፍጥነት ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። 

መተንፈሻ ያጣችው ኮምቦልቻ

ጭንቅንቁ በምግብ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች እና መዝናኛ ቦታዎች ላይም ይስተዋላል። በእነዚህ ቦታዎች የመከላከያ ሰራዊትን ዩኒፎርም የለበሱ ሴት እና ወንድ ወታደሮች መመልከት እንግዳ ነገር መሆኑ ቀርቷል። 

በሰሜን እና ደቡብ ወሎ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ኮምቦልቻ ከተማ እያቀረበ በመጣ ቁጥር፤ በከተማይቱ የሚንቀሳቀሱ የወታደሮች ብዛት ጨምሯል። ጦርነቱ በኮምቦልቻ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች መካሄዱ፤ ወደ ከተማይቱ በቀን ሁለት ጊዜ ይደረግ የነበረውን የአውሮፕላን በረራም አስተጓጉሏል። ረፋድ እና ከቀትር በኋላ ይሰማ የነበረው የአውሮፕላን ማረፍ እና መነሳት ድምጽም ቆሟል።

የኮምቦልቻ ነዋሪዎች ጸሐይ ማዘቅዘቅ ስትጀምር ወደ ቤታቸው ለመግባት ይጣደፋሉ። ምክንያት አላቸው። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከጥቅምት 5፤ 2014 ጀምሮ በጣለው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ምክንያት ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ኃይሎች ውጭ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ አይቻልም። የኮምቦልቻ መንገዶች ከጸጥታ እና የጤና ተቋማት ተሸከርካሪዎች ውጭ በምሽት ማንንም አያስተናግዱም። በዚያ ሰዓት ሲዘዋወሩ መገኘት አደጋን በራስ ላይ መጋበዝ ይሆናል። 

ይህንን ተገንዝቦ አመሻሽ ላይ በጊዜ ወደ ቤታቸው የሚከተቱት የኮምቦልቻ ነዋሪዎች፤ የሰርክ ተግባራቸውን ለማከናወን ወደ ጎዳና እንዲወጡ የሚፈቀድላቸው ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት በኋላ ነው። ነዋሪዎቹ ደጃፋቸው ላይ የደረሰው ጦርነት፤ ህይወታቸውን እንዳያመሰቃቅልባቸው ስጋት እንደገባቸው ፊታቸው ላይ በጉልህ ይነበባል። 

ይህ ስጋት ነዋሪዎቹ በየቦታው በሚያደርጉት ውይይት ውስጥም ይደመጣል። ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆን ያልቻሉት ነዋሪዎች፤ ገንዘብ ለማውጣት ረዣዥም የባንክ ቤት ሰልፎች ላይ ተራቸውን ይጠብቃሉ። እጃቸው ላይ ገንዘብ ያላቸው ደግሞ “የሚሆነው አይታወቅም” በሚል የቻሉትን ያህል አስቤዛ ይሸምታሉ። በሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረትም የህዝቡን የመሸመት አቅም መፈተን ጀምሯል።

የማይቀመሰው የቤት ኪራይ ዋጋ  

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አንደኛ ዓመቱን ሊደፍን ጥቂት ቀናት ቢቀሩትም፤ ኮምቦልቻን ጨምሮ በደቡብ ወሎ የሚገኙ ከተሞችን ወላፈኑ ይገርፋቸው የጀመረው ባለፉት ሶስት ወራት ነው። በአፋር እና በሰሜን ወሎ ባሉ አካባቢዎች ጦርነቱ መበረታት ሲጀምር ከተማይቱ መሸበር ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ሆነች።  

በጦርነቱ ምክንያት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች ወደ ኮምቦልቻ መፍለስ የጀመሩ ተፈናቃዮች ከተማይቱን ማጥለቅለቅ ጀመሩ። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዘሪቱ ሁሴን፤ “በጣም አስደንጋጭ በሚባል መልኩ” ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ይገልጻሉ፡፡ 

እንደ ዘሪቱ ገለጻ በከተማይቱ እስከ ካለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ የነበሩት የመጠለያዎች ብዛት ከአስር የማይበልጥ ነበር። በጥቅምት ወር የመጀመሪያ አስር ቀናት ብቻ ግን እየጨመረ የመጣውን ተፈናቃይ ለማስተናገድ፤ የከተማ አስተዳደሩ አስር ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን ወደ መጠለያ ጣቢያነት መቀየሩን ያስረዳሉ። ወደ ከተማይቱ የሚደረገው የተፈናቃዮች ፍልሰት “በጣም ከምንችለው አቅም በላይ እየሆነ ነው” ይላሉ የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ።

ከተፈናቃዮች ብዛት ማሻቀብ ጋር በተያያዘ በኮምቦልቻ ከፍተኛ ለውጥ ከታየባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የቤት ኪራይ ዋጋ ነው። በከተማይቱ ያለው የቤት ኪራይ ዋጋ  ባለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት ብቻ በእጥፍ ጨምሯል። ላለፉት አስር ዓመታት በቤት ደላላነት የሰራው ሁሴን አህመድም ይህንኑ ያረጋግጣል።  

በከተማይቱ የቤት ኪራይ ዋጋ “መውጣት እና መውረድ” የተለመደ መሆኑን የሚገልጸው ሁሴን፤ ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ወራት በተለይ “መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ” ይስተዋል እንደነበር ይገልጻል። የእዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በእነዚህ ወራት በአፋር ክልል እና በጅቡቲ የሚኖረው ሞቃት የአየር ሁኔታ ሽሽት በርካታ ሰዎች ወደ ከተማይቱ ይመጡ ስለነበር እንደሆነ ያስረዳል። ካለፉት ሶስት ወራት ወዲህ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን፤ ቀድሞ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር “ከፍተኛ ነው” ይላል።  

በተመሳሳይ የስራ መስክ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲሰራ ከድር ፈንታውም በሁሴን ሀሳብ ይስማማል። እንደ ከድር አባባል በከተማይቱ የቤት ኪራይ ዋጋ ከመጨመሩ ባለፈ የሚከራይ ቤት ማግኘቱም አዳጋች ነው። የሚከራይ ቤት ማግኘት የሚቻለው በተለምዶ “የጨረቃ ቤቶች” ተብለው የሚጠሩ መኖሪያዎች ባሉባቸው፤ “ከከተማይቱ ወጣ ያሉ አካባቢዎች ላይ ነው” ይላል።

ሁለቱ የቤት ደላላዎች፤ የቤት ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው ጦርነት የሸሹ ተፈናቃዮች ወደ ኮምቦልቻ መግባት ከጀመሩ በኋላ ነው ባይ ናቸው። ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ቤት ማከራየት የጀመሩት የ47 ዓመቱ አቶ ሰይድ የሱፍም በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ አመላካከት አላቸው። “ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት የተከሰተው በአከራዮች ምክንያት ነው” በሚል በደላሎቹ የሚቀርበውን አስተያየት ግን ውድቅ ያደርጋሉ። “ደላሎች ተፈናቃዮች መሆናቸውን ሲያውቁ ዋጋ ይጨምሩባቸዋል” ሲሉ ተጠያቂዎቹ ደላሎች እንጂ እንደ እርሳቸው አይነት አከራዮች እንዳልሆኑ ይሟገታሉ።

አከራዩም ሆነ ደላላዎቹ የሚስማሙበት ነጥብ ግን የቤት ኪራይ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩን ነው። ደላላው ሁሴን አህመድ ከጥቂት ወራት በፊት እስከ 2,500 ይከራይ የነበረ ቤት አምስት ሺህ እና ስድስት ሺህ ብር ማከራየቱን ይናገራል። ከአራት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ብር ይከራዩ የነበሩ የግቢ ቤቶች፤ በአሁኑ ወቅት ከ8,500 እስከ 10 ሺህ ብር ይጠየቅባቸዋል ይላል። 

በኮምቦልቻ ለዚህን መሰል ከፍተኛ የቤት ኪራይ ጭማሪ መታየት፤ የተፈናቃዮች መብዛት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቢጠቀስም የአካባቢው ባለስልጣናት እና ተፈናቃዮች ዘንድ ግን “ቤት ለመከራየት የታደሉት በቁጥር ትንሽ ናቸው” ባይ ናቸው። በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት መረጃ መሰረት በከተማይቱ 100 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ ባዘጋጃቸው 20 መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ መግባት የቻሉት 30 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።

ሰባ ሺህ ገደማ ከሚሆኑ ቀሪዎቹ ተፈናቃዮች ውስጥ አብዛኞቹ በዘመድ እና በበጎ ፍቃደኞች ቤት ውስጥ መጠለላቸውን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ዘሪቱ ሁሴን ይናገራሉ። በኪራይ ቤቶች ውስጥ ያሉት እጃቸው ላይ ገንዘብ ያላቸው ጥቂት ተፈናቃዮች መሆናቸውንም ያስረዳሉ። ገንዘብም፤ ዘመድም የሌላቸው ተፈናቃዮች ዕጣ ፈንታቸው የቤተ እምነት እና የስብሰባ አዳራሽ ደጃፎች ላይ ማረፍ መሆኑን በሀዘኔታ ይገልጻሉ።

የተፈናቃዮች የበረንዳ ህይወት

የ38 ዓመቱ መሐመድ አህመድ ከኋለኞቹ የተፈናቃዮች ምድብ ውስጥ የሚካተት ነው። መሐመድ 13 ቤተሰቦቹን ይዞ የተፈናቀለው ከሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ነው። አብራው የተሰደደችው ባለቤቱ የስምንት ወር ነፍሰጡር ናት። መሐመድ የደረሰች ባለቤቱን እና ነፍስ ያላወቁ ሁለት ልጆቹን ይዞ የተጠለለው የኮምቦልቻ ከተማ መሰብሰቢያ አዳራሽ በረንዳ ላይ ነው። ዕድሜያቸው የገፋው ወላጆቹ፤ ጎናቸውን ማሳረፊያ እንኳን አላገኙም።

መሐመድ እና ቤተሰቦቹ በአዳራሹ በረንዳ ላይ መዋል፣ ማደር ከጀመሩ ሁለት ሳምንት ሆኗቸዋል። እነ መሐመድ ኮምቦልቻ ከመድረሳቸው በፊት ከሶስት ጊዜ በላይ የመፈናቀል ዕጣ ገጥሟቸዋል። የህወሓት ኃይሎች ራያ እና አካባቢውን ሲቆጣጠሩ ቀዬአቸውን ለቅቀው መውጣታቸውን የሚወሳው መሐመድ፤ ከዚያ ወዲህ በሰሜን ወሎ እና በአፋር ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ከአንድ ቀን እስከ አንድ ወር እየተጠለሉ ኮምቦልቻ መድረሳቸውን ያብራራል። 

ከተደጋጋሚ መፈናቀል በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ከቤተሰቡ ጋር ኮምቦልቻ ከተማ የደረሰው መሐመድ፤ ጭንቀት እና የስጋት ንፋስ የሚነፍስባት ኮምቦልቻ እጇን ዘርግታ አልተቀበለችውም። በኮምቦልቻ ያሉ መጠለያዎች ከእርሱ በፊት በመጡ ተፈናቃዮች በመሞላታቸው፤ እንደ እርሱ መሄጃ ያጡ ከሰሜን ወሎ የመጡ ተፈናቃዮች ጋር መጠጋት ግድ ብሎታል።

ተፈናቃዮቹ የተጠለሉበት ይህ ቦታ የከተማይቱ ዋነኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ነው። የውስጠኛው ክፍሉ ከመሬት ጋር በተያያዙ ወንበሮች የተሞላው ይህ አዳራሽ፤ ተፈናቃዮቹን ለማስተናገድ አልዋለም። በሩም ዝግ ነው። መሐመድን ጨምሮ 400 ገደማ የሚሆኑ ተፈናቃዮች የሰፈሩት በረንዳው ላይ ነው።

ሐሙስ ጥቅምት 11፤ 2014 ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው። በአዳራሹ በረንዳ ደረቅ ወለል ተኝተው ያደሩት ተፈናቃዮች የጥቅምትን ብርድ ለማባረር እሳት አያይዘዋል። ከአዳራሹ በረንዳ ወርደው ቡና የሚቆሉ፤ ሻይ የሚያፈሉ ሴቶችም ይታያሉ። በረንዳው ላይ ምንም አይነት ፍራሽ አይታይም። የአዳራሹን ግድግዳ ተጠግተው የተቀመጡ ብርድልብሶችም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።

ተፈናቃዮቹ ኑሮ እንደከበዳቸው ያስታውቃል። የጥቅምት ብርድ ገጻቸውን ቀይሮታል። አጥንት ድረስ የሚሰማው ቅዝቃዜ የአንዳንዶቹን ድምጽ ዘግቶታል። የተፈናቃዮቹን ይህን ሁኔታ የተመለከተ በአሁኑ ወቅት ለእነርሱ የሚያስፈልገው ቁልፉ ነገር “መጠለያ እና አልባሳት ነው” ብሎ ሊገምት ይችላል። ጠጋ ብሎ ለጠየቃቸው የሚሰጡት ምላሽ ግን ከሁለቱ መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው በባሰ መልኩ “የምግብ ችግር” እንዳለባቸው ሲናገሩ ያደምጣል። 

ተፈናቃዮቹ ለምግብም ሆነ ለሌሎች ችግሮቻቸው በሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ይናገራሉ። እነዚህ ተፈናቃዮች የምግብ እጥረት ችግር እንዳለባቸው የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ይቀበላሉ። “መንግስትም፣ የተራድዖ ድርጅቶችም ትከረታቸው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች ነው። ከመጠለያ ውጭ ያሉ ተፈናቃዮች ትኩረት እየተሰጣቸው አይደለም” ይላሉ።

ከአስቸጋሪው የበረንዳ ህይወት የሚያላቅቀው ቤተ ዘመድ በኮምቦልቻ ከተማ የሌለው መሐመድ፤ አማራጭ ለመፈለግ ዙሪያው ገደል ሆኖበታል። ሁሉንም ቤተሰቦቹን የሚያስተናግድ ቤት ለአንድ ወር ለመከራየት በትንሹ 8,500 ብር ያስፈልገዋል። መሐመድም ሆነ አብሮት የተፈናቀለው ወንድሙ ኑርዬ ግን ይህን ለመክፈል የሚያስችል የገቢ ምንጭ የላቸውም።

በሀብሩ ወረዳ እያለ በአናጢነት እና በቀን ሰራተኝነት ይተዳደር የነበረው መሐመድ፤ ከመፈናቀሉ በፊትም ቢሆን ኑሮው “ከእጅ ወደ አፍ” እንደነበር ይናገራል። አርሶ አደር የሆነው ኑርዬም ያን ያህል የሚያዋላዳ ጥሪት አልቋጠረም። በኮምቦልቻ መሰብሰቢያ አዳራሽ አብረዋቸው የተጠለሉ ሌሎች የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች የኑሮ ሁኔታም ከሁለቱ ወንድማማቾች ጋር ተመሳሳይ ነው። 

“አላህ ፈረጃውን ቅርብ ያድርገው እንጂ…”

“የተሻለ ገቢ አላቸው” የሚባሉትና ወደ ኮምቦልቻ ከመጡ በኋላ ቤት መከራየት የቻሉት ተፈናቃዮች ዘንድም ያለው ብሶት ነው። ወደ ኮምቦልቻ ከመጣ ወር ከአስራ አምስት ቀን ያለፈው ይማም ሀሰን፤ ተከራይተው ከሚኖሩ ተፈናቃዮች መካከል አንዱ ነው። ሶስት የቤተሰብ አባላቱን ይዞ ከሰሜን ወሎ ሀብሩ ወረዳ ወደ ኮምቦልቻ የመጣው ይማም፤ ግቢ ያለው ቤት የተከራየው በስድስት ሺህ ብር ዋጋ ነው። በግቢው ውስጥ እንደ እርሱው ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ አራት ወንድም እና እህቶቹ እንዲሁም ወላጆቹ ይኖራሉ። 

ጦርነቱ በዚህ ቀጠለ “እስከ ዛሬ ስንለፋበት የነበረውን ገንዘብ ጨርሰን ወደ ልመና ነው የምንገባው” ሲል ይማም ስጋቱን ይገልጻል። “እዛ እያለን ስራ እንሰራ ነበር፤ ገቢም ነበረን። እዚህ ወጪ ብቻ ነው” ሲል የሀብሩ እና የኮምቦልቻ ኑሮውን ያነጻጽራል። በእንስሳት እርባታ ሲተዳደር የነበረው ይማም አሁን ያሉበትን ሁኔታ “አላህ ፈረጃውን ቅርብ ያድርገው እንጂ የሚነገር አይደለም” ሲል በምሬት ይገልጸዋል።

ከእርሱ ጋር ተፈናቅለው ኮምቦልቻ ከተማ የሚገኙት ቤተሰቦቹ የራሳቸው ቤት ያላቸው፤ የሞቀ እና የተደላደለ ኑሮ ይኖሩ እንደነበር የሚጠቅሰው ይማም፤ “ንብረታችንን በሙሉ ትተን ነው የመጣነው” ይላል። እርሱን መሰል ተፈናቃዮች አዲስ ለሚከራዩዋቸው ቤቶች የሚገለገሉባቸውን ቁሳቁሶች ለመሸመት ወደ ገበያ ሲወጡ የሚገጥማቸው የሳሳ ኪሳቸውን የሚፈታተን ነው።

በኮምቦልቻ ከተማ በቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ዋጋ ላይ ባለፉት ሁለት ወራት የታየው ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑን ነጋዴዎች ይናገራሉ። ላለፉት 13 ዓመታት በቤት እቃዎች ንግድ ላይ የቆየው አቶ አብዱ ካሳው፤ በማብሰያ እና መመገቢያ እቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ይገልጻል። የጭማሪው ምክንያት የፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን እንዲሁም የትራንስፖርት ችግር መሆኑን ያብራራል።  

ግድግዳው በስዕል ወዳጌጠው የአብዱ የዕቃ መሸጫ ሱቅ ከሚመጡ ተፈናቃይ ሸማቾች ውስጥ፤ አብዛኞቹ የሚጠይቁት ለዕለታዊ መገልገያነት የሚውሉ እቃዎች ዋጋን ነው። አብዱን መሰል ነጋዴዎች “የቅንጦት” ሲሉ የሚጠሯቸውን እቃዎች ዞርም ብለው አይመለከቷቸውም። ትኩረታቸው ለምግብ ማብሰያነት፣ ለመመገቢያነት እና ለውሃ መቅጃነት የሚጠቀሙባቸው እንደ ብረት ድስት፣ ትሪ፣ የውሃ መቅጃ ባልዲዎች ላይ ነው። ነጋዴዎቹ እነዚህን እቃዎች ለኮምቦልቻ ነዋሪ ርካሽ በሚባል ዋጋ የሚያቀርቡ ቢሆንም፤ ተፈናቃዮቹ ግን በቅናሽ ዋጋ ለመግዛት ይደራደራሉ።

ይህን መሰሉ ተፈናቃዮቹ የሚገጥማቸው የኑሮ ፈተና የ30 ዓመቱን ይማም ሆድ ቢያስብሰውም፤ ከዚያ ይልቅ በአሁኑ ወቅት የሚያሳስበው ሌላ ትልቅ ጉዳይ አለ። የሰባት እና የሶስት ዓመት ሴት ልጆቹ ያሉት ይማም፤ ጦርነቱ በልጆቹ ስነ ልቦና ላይ የፈጠረው ጫና ያሰጋዋል። ከእርሱ ጋር ያሉት ወንድሞቹም የራሳቸው ልጆች አሏቸው። የይማም እና ወንድሞቹ ልጆች ስለ አማጽያኑ በየጊዜው የሚያነሱት ጥያቄ እረፍት የሚነሳ ነው። “እዚህም ይመጣሉ እንዴ? ከዚህ ከመጡ ወዴት ነው የምንሄደው?” ለሚለው የህጻናቱ ጥያቄ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት እንደሚቸግረው ይማም ይናገራል። 

ጦርነቱ ገፍቶ ኮምቦልቻ ከደረሰ የቤተሰቦቹ እጣ ፈንታ ጉዳይም ያስጨንቀዋል። “እኛስ እንደምንሆን እንሆናለን። ሴቶቹን እና ህጻናቱን ግን ምንድን ነው የምናደርጋቸው?” ሲል ስጋት አዘል ጥያቄ ይጠይቃል።

የጦርነቱ መቋጫ የሚያሳስባቸው ነዋሪዎች

የኮምቦልቻ ነዋሪዎች እንደ ይማም እና መሐመድ ላሉ ተፈናቃዮች ያላቸው ሀዘኔታ ጥልቅ ነው። በከተማይቱ በተለምዶ ቁጠባ ተብሎ ከሚታወቀው ስፍራ ወደ “ፈን ካፌ” በሚጓዙ ባጃጆች የሚሳፈር ሰው፤ ይህንኑ የነዋሪዎቹን ሀዘኔታ የመታዘብ እድል ያገኛል። ባጃጆቹ በመሄዱበት መንገድ ላይ የኮምቦልቻ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ይገኛል። ተሽከርካሪዎቹ ከአንድ ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ተጠልለውበታል የሚባለውን ትምህርት ቤት ሲያልፉ ከተሳፋሪዎች ሀዘኔታ የተቀላቀለበት ንግግር ይሰማል።

ሀዘኔታቸው ለተፈናቃዮች ነው። ነገር ግን እዚያ ላይ አያቆምም፤ ሀዘኔታ እና ርህራሄው ለራስም ነው። የኮምቦልቻ ነዋሪዎች፤ ጦርነት የሰሜን ወሎ ዞን ነዋሪዎችን ህይወት እንዴት እንደቀየረው አይቷል። የጦርነት ዳፋው እስከምን ድረስ እንደሆነ ታዝቧል። ጦርነት ከመጣ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የመኖሪያ ቀዬን ጥሎ መሸሽ እንደሚያስከትል ከሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች ተመልክቷል።

ዛሬ የተፈናቃይ አስተናጋጅ የሆኑት የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ ነገ በተራቸው ተፈናቃይ እንዳይሆኑ ስጋት ገብቷቸዋል። ይህን ስጋት ለመላቀቅ ደግሞ ብቸኛው መፍትሔ ጦርነቱን በፍጥነት ማጠናቀቅ ነው የሚል እምነት አላቸው። ሐጂ ሁሴን መሐመድ ይህን አመለካከት ከሚያራምዱ የኮምቦልቻ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።

የ65 ዓመቱ አዛውንት፤ የመውሊድ በዓል በተከበረበት ዕለት ከአምስት ወጣቶች ጋር ተቀምጠው በወቅታዊው የጦርነት ሁኔታ ላይ ሲወያዩ ያንጸባረቁት ሀሳብም ይህንኑ ነበር። ቀበሌ ስምንት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በምትገኝ ትንሽ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ አጠገብ ካለ ዛፍ ስር ይካሄድ በነበረው ውይይት የተለያዩ ሀሳቦች ቢንሸራሸሩም፤ ይበልጥ ጎልቶ የወጣው ግን እርሳቸው ይደግፉት የነበረው ሀሳብ ነው። 

ሐጂ ሁሴን ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባዋል የሚሉት በአካባቢው ሰላም ማስፈንን ነው። ሰላም ሊመጣ የሚችለው ወደ ጦር ግንባር ሂዶ በመዋጋት እንደሆነ ይገልጸሉ። “የክተት ጥሪ ተደርጎልን እንደ እነሱ እኛም ተነስተን ወደ ግንባር እንሂድ። ወንድሞቻችን በየጫካ እየወደቁ ነው። እኛም መውደቅ አለብን። መሞታችን ስለማይቀር ተፋልመን እዛው እንሞታለን” ይላሉ በያዟት ከዘራ መሬቱን እየመቱ።

በደላላነት የሚተዳደረው ሁሴን አህመድም የእዚህ ሀሳብ አቀንቃኝ ነው። የደላላነት ስራ ከመጀመሩ በፊት የመከላከያ ሰራዊት አባል የነበረው ሁሴን ከ20 ዓመታት በፊት በነበረው ደም አፋሳሹ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ተሳትፏል። ከመሳተፍ ባለፈም በጦርነቱ እግሩ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምርኩዝ ለመጠቀም ተገድዷል። እንዲያም ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ጦርነት ለመግባት እንደማያመነታ ይናገራል። “ቤትህ እየተቆረቆረ ከምትገደል [ወደ ጦርነቱ] መሄድ ነው የሚሻለው” ይላል የሁለት ልጆች አባት የሆነው ሁሴን። 

የሚያሽከረክራትን ባጃጅ መንገድ ዳር አቁሞ ሐጂን እና ወጣቶቹን የተቀላቀለው ጀማል የተባለ ወጣት፤ ጦርነቱን ባለበት ከዚም በላይ መደረግ አለበት ይላል። እንደ እርሱ እምነት ጦርነቱ በቶሎ እንዲያልቅ፤ “እድሜው የደረሰ ሁሉ ወደ ጦርነቱ እንዲገባ መደረግ አለበት”። ከዚህ ውይይት በኋላ ባሉት ተከታታይ ቀናት፤ የእነ ጀማልን እምነት የሚጋሩ የሚመስሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች፤ በጭነት ተሽከርካሪዎች ተጭነው ወደ ጦር ግንባር ሲዘምቱ ታይተዋል። 

ወጣቶቹ በእጃቸው በጣት የሚቆጠሩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን የያዙ ናቸው። በብዙዎቹ እጅ በርክቶ የሚታየው ገጀራ እና ዱላ ነው።   ወኔያቸው ከፊታቸው የሚነበበው እነዚህ ወጣቶች፤ አማጺያኑን ለመግታትእየዛቱ ከከተማይቱ ሲወጡ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሚደመጡት አንድ ሀረግ አለ-  “በድል እንመለሳለን” የሚል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)