ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን፤ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ለማጥቃትም ሆነ ለመክበብ የሚያደርጉትን ማናቸውም እንቅስቃሴ እንደሚቃወሙ አንድ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣን አስታወቁ። የህብረቱ የውጪ ግንኙነት ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ይህን ያሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ “ህልውና እና ሉዓላዊነት” ላይ ተደቅኗል ያለውን “አደጋ ለመከላከል” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በደነገገበት በዛሬው ዕለት ነው።
ቦሬል በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር መልዕክት፤ “አዲስ አበባን ለማጥቃትም ሆነ ለመክብብ በህወሓት ወይም በኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚደረግ ማንኛውንም እርምጃ እንቃወማለን” ሲሉ የአውሮፓ ህብረት አቋምን ግልጽ አድርገዋል። በኢትዮጵያ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአውሮፓ ህብረት “ደንግጧል” ያሉት ቦሬል፤ ሁሉም ወገኖች ሰላምን ለመቀበል ዕድል እንዳላቸው ገልጸዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ በተደነገገበት በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ የሚገኙ አሜሪካውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ማድረግን እንዲያስቡበት ምክር ለግሷል። ወደ ኢትዮጵያ የመጓዝ ዕቅድ ያላቸውም ቢሆኑ ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ ጥቆማ ሰጥቷል። ኤምባሲው በፌስቡክ በኩል ባሰራጨው መግለጫ ሰራተኞቹ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደማይጓዙም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)